አቶ ሽታሁን ዋለ
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በሀገሪቱ ቀዳሚና በህትመቱ ዘርፍ ከ100 ዓመት በላይ አገልግሎት እየሠጠ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በህትመት አገልግሎቱ ከምስረታ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ከፍተኛ ሲሆን፤ ድርጅቱ የተለያዩ መፅሐፍቶችን፣ ጋዜጦችን፣ መፅሄቶችንና ሌሎች የተለያዩ ሚስጢራዊና መደበኛ ህትመቶችን በማተም ለትምህርት መስፋፋት፣ ለወቅታዊ መረጃዎች ስርጭት እና ለሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መቀላጠፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዘርፉ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማርካትና በሚታየው የገበያ ውድድር ወስጥ የተሻለና ተመራጭ ለመሆን አቅም የማሳደግ ሥራዎች በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በህትመት ዘርፉ በየጊዜው የተፈጠሩትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር ሰራተኞች እንዲተዋወቁ ለማድረግ በየጊዜው የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱ በማድረግ በኢንዳስትሪው ላይ ተወዳዳሪ ለመሆንና የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ ከመደበኛ ህትመት በተጨማሪ የሚስጢራዊ ህትመት ስራዎችን በመስራት ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን የተለያዩ ሚስጢራዊ ይዘት ያላቸው ህትመቶች በማተም የውጭ ምንዛሪ በማዳን በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝና አሁንም በውጭ እየታተሙ የሚገኙትን የመደበኛና የሚስጢራዊ ህትመቶች በድርጅቱ እንዲታተሙ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ለማዳን የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡
ድርጅቱ የውስጥ ሰራተኞች አቅም ለማሳደግና በአገር አቀፍ ደረጃ በህትመት ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በማቋቋም በሶስት የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ማለትም በህትመት ቴክኖሎጂ፣ በግራፊክስ ዲዛይንና ኤዲቲንግ እና በሥራ ቅበላና የህትመት ዋጋ ትመና ከደረጃ አንድ እስከ ሶስት እንዲሁም የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን ፈቃድ በማግኘት የረዥም ጊዜ ልምድና ብቃት ባላቸው አሰልጣኞች ስልጠናዎችን በመስጠት በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ኮሌጁ በተቋማት ልዩ ፍላጎት መሰረት የተለያዩ ስልጠናዎችንና የምክርና የጥገና አገልግሎት ይሠጣል፡፡
ድርጅቱ የገበያ አማራጭ በመፍጠር ገቢን ለማሳደግ እና ደራሲያንን ለማበረታታት የአሳታሚነት ስራን ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት አጋዥ የሆኑ መፅሐፎችን፣ የህጻናት መጻህፍት እና ልቦለዶች በማተም ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡
ከህትመት ስራው በተጨማሪ ድርጅቱ በአካባቢው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ለአካባቢ ፀጥታና ደህንነት፣ማህበራዊ አገልግሎት ላይ እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች እና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጥሪዎች ላይ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ አድርጓል፤ በቀጣይም አቅሙ በሚፈቅደው አግባብ የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
ድርጅቱ በ2022 ዓ.ም በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ የህትመት ተቋም ለመሆን እና እየሰጠው ያለውን የህትመት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል በማጎልበት በህትመት ዘርፍ የሚታየውን የገበያ ውድድር በማሸነፍ የመሪነት ሚናውን አስጠብቆ ለመቀጠል፣ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ ለማርካትና አዳዲስ የቢዝነስ ሐሳቦችን በማመንጨት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ ለማድረግ የሠራተኛው፣የሠራተኛ ማህበሩ፣ የማኔጅመንቱ እና የሥራ አመራር ቦርድ በቁርጠኝነትና በቅንጅት መንቀሳቀስ እንዳለብን እያስገነዘብኩ የደንበኞቻችን ትብብርና የመንግስት እገዛ ከጎናችን እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
አመሰግናለሁ!