ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ በህወሓት አሸባሪ ኃይል የተከፈተባትን ጦርነት ለመቀልበስ በሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተከፈለ ላለው መስዋትነት እና ተጋድሎ የድርጅቱን ደጀንነት የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑ ተገልፀ፡፡

ታህሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስርያ ቤት በተካሄደው የርክክብ ስነ-ስርዓት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ተገኝተው በየኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የፋይናንስ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤት ለሆኑት ለክብርት ወ/ሮ ማርታ ሊዊጂ ቼኩን አስረክበዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ቀደም ሲል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በሁለት ዙር አምስት ሚልዮን አምስት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉንና ድርጅቱ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድርግ ለበዓሉ ዝግጅት የተያዘውን በጀት በመቀነስ፤ የድርጅቱ አመራሮችና ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን መዋጮ በማድረግ፣ የድርጅቱ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበርም ከተቀማጭ ወጪ መማድርግ እና የሰራተኞች የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበርም በበተመሳሳይ መዋጮ በማድረግ ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው በደቡብ ጎንደር፣በደቡብ ወሎና በአፋር ለሚገኙ ወገኖች በዓይነት ቦታው ድረስ በመገኘት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በእለቱም ለመከላከያ ሰራዊቱ አራት ሚልዮን አምስት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ በስፍራው መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ከተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል ወደ ግንባር በመዝመት ጠላትን ለመፋለም ዝግጁ የሆኑ ሃያ ሶስት የድርጅቱ ሰራተኞች መመዝገባቸውንና በሚመለከተው አካል የሚሰጠውን አቅጣጫ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በተያያዘም መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት ወረዳ ዘጠኝ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት እየተካሄደ ላለው የበዓል ማክበሪያ በሬ ማሰባሰብ ሥራ ሁለት ሰንጋ በሬዎችን መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በድምሩ አስር ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አቶ ሽታሁን ዋለ ጠቁመዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የፋይናንስ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለበዓል አከባበሩ ሊወጣ ከነበረው ወጪ ላይ በመቀነስ እንዲሁም ከሰራተኛውና አመራሩ የተለገሰን ገንዘብ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊትና በጦርነቱ ለተጎዱና ለፈፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጋቸው የሚያስመሰግንና አንጋፋው ድርጅት የሀገር አልኝታነቱን ያስመሰከረበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱን የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያሳሰቡት ሚስትር ዴኤታዋ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ላከናወነው አርዓያነት ያለው ተግባር በሰራዊቱ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡