የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ተገመገመ

ድርጅቱ በግማሽ ዓመት ያስመዘገበውን አበረታች ውጤት አጠናክሮ በመቀጠል የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት ሁሉም በጋራ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የድርጅቱን የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወር የኦፕሬሽንና የለውጥ ስራዎች ዕቅድ አፈፃፀም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል መሰብሰብያ አዳራሽ ተገመገመ፡፡ በግምገማው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ አብዱረህማን ዒድ ጣሂር እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኦፕሬሽን፣የፋይናንስ፣የሪፎርም፣ ኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ የፕሮጀክትና ማህበራዊና አካባቢያዊ ግዴታዎች አፈፃጸም እንዲሁም በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት በድርጅቱ የዕቅድ ዝግጅት ፕሮጀክት ጥናትና ክትትል አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ መኮንን አበራ በኩል ቀርቧል::

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ውስጥ የኦፕሬሽን ፣የፋይናንስ ፣የፕሮጀክት/ኢንቨስትመንት ፣የሪፎርም ሥራዎች፣የኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ማህበራዊ ኃላፊነት እና ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች አፈፃፀሞች በተመለከተ ድርጅቱ በ6 ወር ወስጥ የነበረውን አፈፃፀም ግምገማ ግብረ መልስ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር የሆኑት ቃልኪዳን አረጋ በኩል በዝርዝር ቀርቧል፡፡

ድርጅቱ ከተቀመጠው የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ አስቀድሞ የሚልክ መሆኑን እና የሪፖርት አቀራረቡ በተመለከተ በተላከው ፎርማት መሰረት በግልፅ ተብራርቶ እና የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ በዝርዝር የሚያሳይ እና አስፈላጊውን መረጃ የያዘ እና በጥራት ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑን በግብረ መልሱ ላይ ተገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃጸም ግምገማ ላይ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተግባራዊ እንዲደረጉ አቅጣጫ የተሰጣቸው ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት መደረጉም በግምገማው ላይ ተገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ ያጋጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቹን በመቋቋም ገበያ ላይ መቆቱና ችግሮቹን ለመፍታት ባደረጋቸው ጥረቶች፣ በምርት፣ በሽያጭና በፋይናንስ አፈፃፀም ጠንካራ በመሆኑ ወደ ተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እና  ማስፋፍያ ስራዎችን የገባበት ሂደት የሚበረታታ መሆኑን በግብረ መልሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በሚስጢራዊ ህትመት እና በልዩ ልዩ ህትመቶች አፈፃጸም ከእቅድ አንፃር በልጦ መከናወኑ፣ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ሚስጢራዊ ህትመቶች በትርፍ ሰዓት ጭምር ተሰርቶ በጊዜ ማስረከብ መቻሉ፣መለዋወጫዎችን በሞዲፊክ በመስራትና በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ አምጥተው ከሚሸጡ አቅራቢዎች መለዋወጫዎችን በመግዛት ማሽኖቹ ጠግኖ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉ እና ከውጭ አገር ባለሙያዎችን በማስመጣት ማምረቻ መሳሪያዎችን አስጠግኖ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጋቸው በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ድርጅቱ ካከናወናቸው መልካም አፈፃፀሞች መሆናቸውን በግብረ መልሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

የድርጅቱ የገቢ አፈፃጸም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ሽያጭ በ34.8 % እንዲሁም ትርፍ በ26.4 % ከእቅድ ከፍ ብሎ መከናወኑ በጠንካራ ጎን የተገመገመ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ተገልፀዋል ፡፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ (EIH) ከሚከታተላቸው ድርጅቶች ውስጥ IFRS ተግባራዊ ካደረጉ ጥቂት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን እና ሂሳብ ወቅታዊ ማድረግ መቻሉ ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ የሆነና ተሞክሮ የሚወሰድበት ድርጅት መሆኑን በመገንዘብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገልፀዋል፡፡

በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የህትመት ስራዎችን እንዳይቆሙ ግብዓቶችንና መለዋወጫዎችን ከአገር ውስጥ አምራቾች እና አቅራቢዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ አስመጥተው ክፍያው በብር እንዲከፈላቸው በመነጋገርና በማግባባት ግዥ በመፈፀም ችግሮችን ለመፍታት ጥረት መደረጉ፣ቼክ ፐርሰናላይዜሽን ለመስራት የሚያገለግሉ አራት የማምረቻ መሳርያዎችን ማስገባት መቻሉ፣ ዲጂታል የፈተና ህትመት መስሪያ ማሽን ለመግዛት የጥናት ሰነድ ማዘጋጀትና አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መስራት፣በሽርክና ለሚሰሩ ስራዎች ድርጅቱ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ መቻሉና የ2014 በጀት ዓመት ሂሳብ በወቅቱ መዘጋቱና  ከስህተት የፀዳ መሆኑ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ድርጅቱ ካከናወናቸው ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን በግምገማው ተገልፃል፡፡

በእቅድ የተያዘውን የመፅሐፍ ህትመት ስራ ከእቅድ በታች አፈፃጸም የተመዘገበ መሆኑና በቀጣይ እቅድ ሲያዝ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት፣የጋዜጣ ህትመት የቅጅና የገፅ ብዛት መቀነስ የሚታይ በመሆኑ ይህን ችግር ለመፍታት ኦንላይን የጋዜጣ ህትመት ላይ መስራት እንዲሁም በማሸኖች እርጅና ምክንያት እና በወቅቱ ማሽኖቹን ጠግኖ ወደ ስራ ባለማስገባት የደንበኞችን ህትመት በጊዜ ከማስረከብ አንፃር ክፍተት የሚታይ በመሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ስራዎችን መቀበል እና ደንበኞችን ላለማጣት በቅናሽ ዋጋ በማተም ደንበኞችን ማርካት በቀጣይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን በግብረ መልሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የኢንቨስትመንት ጉዳዮች በመለየት በእቅድ ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ ማድረግ፣አዳስ ለሚገቡ ቴክኖሎጂዎች በተሳካ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ወቅታዊ የሆነ የድርጊት መርሃ-ግብር ማዘጋጀት እና አዳዲስ ለሚታሰቡ ሥራዎች እና በሽርክና ለሚከናወኑ ስራዎች ድርጅቱ ካለው የረጅም ጊዜ ልምድና ተሞክሮ የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል በእቅድ ላይ ተመስርቶ የሰው ሃይል ማዘጋጀት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን በግብረ መልስ ሪፖርቱ ላይ ተገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ብዙ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ሪፖርት ማውጣት የሚችል ሲስተም አሁን ካለው በላይ ተግባራዊ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ተገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በድርጅቱ ላይ ብዙ ኢንቨስትመንት ለማካሄድ የታሰበ በመሆኑ የፋይናንስ ሪፖርቱ ወቅታዊ ማድረግ እንደሚገባና ኢንቨስት ለማድረግ በሚደረገው ድርድር ላይ የፋይናንስ ሪፖርቱ ላይ ክፍተት ካለ ድርጅቱም ሆነ EIH ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም የማሳጣት እድል ስላለው ትክክለኛ የሆነ ዳታ በመያዝ ድርጅቱ ራሱን ብቁ ማድረግ እንደሚገባ በግምገማው ላይ ተመላክቷል፡፡

በተወሰኑ የቢዝነስ መስኮች ላይ ስትራቴጂክ ጥናት ማካሄድ፣አዳዲስ ከሚመጡ ኢንቨስትመንቶች አሁን ያለውን የድርጅቱ አሰራርና ቴክኖሎጂ ወቅታዊ ማድረግ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግ በ2016 በጀት ዓመት እቅድ ዝግጅት ላይ ታሳቢ ተደርጎ እንዲዘጋጅ በግብረ መልሱ ላይ ተገልፀዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ አብዱረህማን ዒድ ጣሂር  እንደተናገሩት ድርጅቱ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ የግማሽ ዓመቱን እቅድ አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ ማከናወኑን ገልፀው ለአፈፃፀሙ ውጤታማነት የቦርዱ ፣የማኔጅመንቱና የሰራተኞች የተቀናጀ ስራ የጎላ ሚና እንደነበረው ገልፀዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አያይዘውም ድርጅቱ ሂሳቡን በIFRS መሠረት ተመርምሮ በወቅቱ መዝጋት እና በውጭ ኦዲት ተመርምሮ ሪፖርት መቅረቡ እና የኦዲት አስተያየቱም ከስህተት የፀዳ መሆኑ ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ መሆኑን ጠቅሰው ለቀጣይ ድርጅቱ ለሚያከናውነው ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንና ይህን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ድርጅቱ ካሉት የልማት ድርጅቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው ያለውን ሀብት ኢንቨስት በማድረግ ስራዎችን በማስፋፋትና ተጨማሪ አዳዲስ ስራዎችን በመፍጠር ተጨማሪ ሀብት መፍጠር፣ድርጅቱ ከህትመት ጋር ያልተገናኙ ሌሎች ተጨማሪ ገቢዎችን የሚገኝበት ሁኔታ መፍጠር፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መስራት፣ የገበያ ምንጭ ማስፋት፣የደንበኞችን ስራ በጥራት መስራት እና የማስረከቢያ ጊዜ መጠበት እንዲሁም በሰራተኛ ማህበር አመራሮችና አባላት መካከል የተፈጠረውን ችግር መፍታት  ለቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ 6 ወር ውስጥ ያስመዘገበውን ውጤት አበረታች መሆኑን የገለፁት አቶ አብዱረህማን በቀጣይ በግማሽ ዓመቱ የታዩትን ክፍተቶች በማስተካከል የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም ድርጅቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ያጋጠመውን የማምረቻ መሳርያዎች ግዥ ችግር ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ መስራቤታቸው ማንኛውም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ በግማሽ ዓመት ውስጥ ብር 176,347,234 የሚያወጣ ምርት ለማምረት አቅዶ አፈፃፀሙ ብር 274,329,902 የሚያወጣ ምርት ለማምረት በመቻሉ አፈጻጸሙ 155.56 %  ሲሆን፣ ከተጣራ ሽያጭ ብር 345,778,890 ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ክንውኑ ብር 466,274,548 ሲሆን አፈጻጸሙ 134.85% ሆኗል፡፡ ከታክስ በፊት ብር 121,387,028 ትፍር ለማግኘት ታቅዶ ክንውኑ ብር 153,429,532 ሲሆን አፈፃፀሙ 126.40% መሆኑ   ይታወቃል፡፡