በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በዋናነት ለጋዜጣ ህትመት ሥራ እየዋለ የሚገኘው ፕሪማ 578 ህትመት ማሽን ላይ መሰረታዊ ጥገና በመደረጉ አዎንታዊ ለውጥ መመዝገቡ ተገለፀ

ወቅቱን የጠበቀ ጥገናና ሰርቪስ የድርጅቱን ምርታማነትን ከመጨመርም በላይ የማሽኖችን የአገልግሎት ጊዜ  በማስረዘም ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተነግሯል፡፡

ድርጅቱ ለህትመት ከሚጠቀምባቸው ማሽኖች መካከል ፕሪማ 578 እና 546 ማሽኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡  ማሽኖቹ በዋናነት የጋዜጣ ህትመት እንዲሰራባቸው ታሳቢ ተደርጎ በ2008 ዓ.ም ወደ ድርጅቱ የገቡ ሲሆን ባለ ሙሉ ቀለም ህትመትን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ማሽኖቹ በድርጅቱ ተተክለው የህትመት ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እጅግ በርካታ የህትመት ውጤቶችን በማተም በድርጅቱ ምርታማነት ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ቢሆንም ረዘም ላለ ጊዜ ከማገልገል ጋር ተያይዞ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በህትመት ጥራት ላይ፣የጥሬ ዕቃ ብክነትና የህትመት ውጤቶችን በሚፈለገው ጊዜ ከማድረስ አንፃር ችግሮች ነበሩ፡፡ በህትመት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ደግሞ ድርጅቱ ከአንጋፋ ደንበኞቹ ጋር ያለውን የጠበቀ መልካም የሥራ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠራቸውም ባሻገር  በኦፕሬተሮች እና ቴክኒክ ባለሙያዎች የሚኖረው ጫና እጅግ የጎላ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡

የደንበኞችን ቅሬታና አስተያየት እንዲሁም በየጊዜው በማተሚያ ማሽኖች አቅምና አፈፃፀም ላይ የሚደረገውን ክትትልና ግምገማ መነሻ በማድረግ ማሽኖቹ መሰረታዊ ጥገናና ሰርቪስ ሊደረግላቸው እንደሚገባ መወሰኑን የድርጅቱ የመደበኛ ህትመት ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ገ/ወልድ ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ዳኛቸው ገለፃ ፕሪማ 546 እና 578 ሥራ የጀመሩት በ2008 ዓ.ም እንደነበር እና ጋዜጣና መጻህፍት ህትመት ይታተምባቸው እንደነበር አስታውሰው በወቅቱም አንድ አዲስ ማሽን ሊኖረው የሚገባወን የማተም አቅም እንደነበራቸው ያስረዳሉ፡፡

ለህትመት ማሽኑ ጥገና እንዲደረግ ከታመነበት በኋላ በድርጅቱ የግዢ ስርዓት መሰረት ጨረታ አውጥቶ ጥገናውን የሚያከናውን ተቋም መለየት እና አጠቃላይ የቅድመ ጥገና ሥራዎችን ማከናወን በቅንጅት የተሰሩ ስራዎች እንደነበሩ አቶ ዳኛቸው ገልፀው የጥገና ሂደቱ ደረጃ በደረጃ ሂደቱን ጠብቆና አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገበት መካሄዱን ያብራራሉ፡፡

ለህትመት ማሽኑ ጥገናና ሰርቪስ መደረጉ ከጥራት፣ብክነትን ከመቀነስና፣ የህትመት ውጤቶችን በወቅቱ ከማስረከብ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለው የገለፁት ዳይሬክተሩ ደንበኞች በጥራትና በጊዜ ከመረከብ አንፃር ሲያነሱት የነበረውን ቅሬታ አስቀርቷል ብለዋል፡፡

በድርጅቱ ከፍተኛ የህትመት ባለሙያ የሆኑት አቶ አሚሮ ያሲን በበኩላቸው የማሽኖች ጥገና በድርጅቱ እና በውጪ ባለሙያዎችን እንደሚከናወን ገልፀው ለፕሪማ 578 ህትመት ማሽን በውጭ ባለሙያዎች ሙሉ ጥገና ተደርጎለታል ብለዋል፡፡

አቶ አምሩ ጥገናው ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ በፕሪማ 578 ይሰራ የነበረው የጋዜጣ ህትመት ሥራ የጥራት ጉድለት ይታይበት ስለነበረና የጥራት ጉድለቱም ከደንበኞች ጋር ያለመግባባት የሚያስከትል በመሆኑ እንዲሁም ማሽኑ በሚፈለግበት ወይም ሙሉ አቅሙን መጠቀም እንዲቻል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ማሽኑ ጥገና ሳይደረግለት የነበረውን የጥራት ችግር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደርጃ ተቀርፎ የተሻለ ማተም መቻሉንና የድርጅቱን የህትመት እና የጥገና ባለሙያዎችን ከከፍተኛ ድካም ታድጓል ተብሏል ፡፡

በተመሳሳይ ረዳት የህትመት ባለሙያ የሆኑት አቶ ያዕቆብ እውነቱ በማሽኑ ላያ የተስተዋለውን ለውጥ መልካም እንደሆነ ጠቁመው በቀጣይም የጥገናና የሰርቪስ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ይገልፃሉ፡፡

ተጠግኖ አመርቂ ውጤት የሰጠውን ፕሪማ 578  መነሻ በማድረግ በቀጣይ ፕሪማ 546 በተመሳሳይ ለማስጠገን ዕቅድ መያዙንና ወቅቱን የጠበቀ ጥገናና ሰርቪስ የድርጅቱን ምርታማነት ከመጨመርም በላይ የማሽኖችን የአገልግሎት ጊዜ  በማስረዘም ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አቶ ዳኛቸው ተናግረዋል፡፡