የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ህፃናት ማቆያ ማዕከል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

 

ልጆቻቸውን በህፃናት ማቆያው የሚያውሉ እናቶች አገልግሎቱ ከበርካታ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጫናዎች እንደታደጋቸው ይገልፃሉ፡፡

ሠራተኞች ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ሁኔታዎች በሥራቸው ውጤታማነት ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡  የፆታ እኩልነት በተከበረበት በአሁኑ ወቅት ሴቶች ከወንዶች እኩል በመረጡት የሥራ መስኮች ተሰማርተው ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ሴቶች በተፈጥሮ የተጎናፀፉት ፀጋ (እናትነት) ከእርግዝና ጀምሮ ልጅ ወልዶ የመንከባከብ ኃላፊነት ራሱን የቻለ ከፍተኛ ዋጋ የሚከፈልበት ነው፡፡ ሴቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች መሰማራታቸውን በተፈጥሮ ካሉባቸው ኃላፊነቶች ጋር ተደምሮ ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር ያሉትን ጫናዎች ከፍ ያደርጓቸዋል፡፡ በሀገራችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሴት ሰራተኞችን በሥራዎቻቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከሚያስችሏቸው ጉዳዮች መካከል በቤት ህፃናት ልጆችን ከመንከባከብ  ጋር ተያይዞ ያሉትን ጫናዎች ለማቅለል በሥራ ቦታዎቻቸው  ህፃናት ማቆያ ማዕከል እንዲከፈቱ መደረጉ ነው፡፡

በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትም ከመስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የህፃናት ማቆያ ማዕከል ተከፍቶ ሥራ መጀመሩን የድርጅቱ ስርዓተ ፆታ ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሃይማኖት ገልፀዋል፡፡   እንደ ወ/ሮ ሄለን ገለፃ  በድርጅቱ ስርዓተ ፆታ ፅ/ቤት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ ሴት ሰራተኞችን ማብቃት እንደሆነና የህፃናት ማቆያ ማዕከሉም መከፈት በቀጥታ ሴቶች ያሉባቸውን የተደራረቡ ጫናዎች ለማቃለል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የማዕከሉ መከፈት ህፃናት ልጆቻቸውን በማቆያው ለሚያውሉ እናቶችም ሆነ ለድርጅቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የፅ/ቤት ኃላፊዋ ይገልፃሉ፡፡ ለእናቶቹ ጫናዎቻቸው ተቀንሰው በተረጋጋ መንፈስ ሙሉ ትኩረታቸውን ስራቸው ላይ አድርገው ሲሰሩ በተመሳሳይ ልጆቻቸው በህፃናት እንክብካቤ ሙያ ዘርፍ በሰለጠኑ ባለሙያዎች አስፈላጊው ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መቆየት መቻላቸው እንዲሁም እናቶች በተወሰነ የሰዓት ልዩነት ልጆቻቸውን መጎብኘት መቻላቸውና ለሚጠቡ ህፃናት ማጥባት መቻላቸው ሲሆን ለድርጅቱ ደግሞ የምርት ሰዓቱ ተጠብቆ የተሻለ ምርታማ መሆን  እንዲችል ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ህፃናቱ በማዕከሉ በሚቆዩበት ጊዜ በሰዓት የተከፋፈለ መርሃ ግብር መኖሩን የጠቆሙት ወ/ሮ ሄለን ልጆቹን ከመረከብ ጀምሮ የዕንቅልፍ ፣የመጫወቻና የመመገቢያ ሰዓት እንዳላቸው እና ለመጫወቻነት የሚውሉ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለማሸለቢያ የሚውሉ ፍራሾች ንፅህናቸው ተጠብቆ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል፡፡

በማዕከሉ አሁን ላይ 13 ህፃናት አገልግሎቱን እያገኙ እንደሆነና በቀጣይም ማዕከሉ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ ሄለን ገልፀው እድሜያቸው ከአራት ዓመት በታች ህፃናት ያሏቸው የድርጅቱ ሴት ሰራተኞች የማዕከሉን አገልግሎት እንዲጠቀሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በማዕከሉ ልጆቻቸውን ከሚያቆዩ የድርጅቱ ሰራተኞች መካከል ወ/ሮ ዮርዳኖስ ዘርፍነህ በሰጡት አስተያየት የህፃናት ማቆያ ማዕከሉ ከከፍተኛ የስነ-ልቦናና የኢኮኖሚ ጫና እንደታደጋቸው ገልፀው ማዕከሉ አገልግሎት በማይሰጥበት ጊዜ ልጆችን ቤት ማዋሉ ሥራን በተረጋጋ መንፈስ ለመስራት ፈተና እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡ አክለውም ማዕከሉ ተከፍቶ ሥራ መጀመሩንና የእናቶችን ጫና ማቃለሉን በመጠቆም ድርጅቱንና በማዕከሉ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን ባለሙያዎች አመስግነዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌላኛዋ ተጠቃሚ የድርጅቱ ሰራተኛ ወ/ሮ ፀዳለ ቡልቻ በበኩላቸው በድርጅቱ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው በማዕከሉ እንዲውሉ ሲደረግ በሞግዚቶቹ ከሚደረግላቸው ሙያዊ እንክብካቤ ባሻገር በእረፍት ሰዓት ሁኔታቸውን ለመከታተል መቻሉ ከልጆቹ ጋር አብሮ የመዋል ያህል ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ገልፀው የድርጅቱን የሥርዓተ ፆታ ፅ/ቤት ኃላፊና የህፃናት እንክብካቤ ባለሙያዎቹን አመስግነዋል፡፡