ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የISO 9001፡ 2015 የዓለም አቀፍ ጥራት ስራ አመራር ሥርዓት ሠርተፍኬት ለስድስተኛ ጊዜ አግኝቷል   

የዕውቅና ሠርተፍኬቱ ድርጅቱ የISO 9001፡ 2015 የዓለም አቀፍ ጥራት ስራ አመራር ሥርዓትን ለማስቀጠል የሚያስችል ብቁ ቁመና ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

 

የISO 9001፡ 2015 ጥራት ስራ አመራር ሥርዓት የአንድን ድርጅት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን ቁልፍ ሚና ያለው የአሰራር ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉት የጠቀሱት የድርጅቱ ጥራት ሥራ አመራርና ማረጋገጫ ቡድን መሪ አቶ በድሉ ሴብሮስ ሥራው በውዴታ እና በተነሳሽነት እንዲተገበር በማድረግ በጥሬ ዕቃ፣ ግዥና አቅርቦት እንዲሁም በማምረት ሂደት የሚኖርን ሥጋት በሥርዓት ለመፍታት ከማገዙም ባሻገር በምርቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶችን በቀላሉ ምላሽ በመስጠት ትርፋማ በመሆን ተቋሙን ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል፡፡ በተያያዘም የአሠራር ሥርዓቱ ሥራዎች ግልጽና ጥራት ያለው ሁሉም የሚተማመኑበት ስርዓት እንዲዘረጉ  የሚያደርግ፤ ደንበኞቻችንም በየጊዜው አሰራራችንን የሚያውቁትና እንዲተማመኑበት የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ያገኘው ሠርተፍኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው በሦስተኛ ወገን የተረጋገጠ እንደሆነና በእውቅናው በመበረታታት በእያንዳንዱ የምርት ሂደት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ቀጣይነት ያለው የለውጥና የምርት ማሻሻያ ሥርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ክፍተቶቻችን ላይ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ መስራት ከድርጅቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪው ገለፃ ይህን ሠርተፍኬት በማግኘታችን የጎደለን ነገር የለም ማለት እንዳልሆነና በውጭም ሆነ በውስጥ የISO 9001፡ 2015 ጥራት ስራ አመራር ሥርዓት ኦዲተሮች የሚሰጡ ማሻሻያዎችን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም በኦዲት ወቅት የሚታዩት ወይም የሚወሰዱት ጉዳዮች ሳምፕል በመሆናቸው በተዘጋጁ መመሪያዎች፣ ኘሮሲጀሮችና ቼክሊስቶች መሰረት መስራት  የISO 9001፡ 2015 የጥራት ስራ አመራር ሥርዓትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የአሰራር ማሻሻያዎችን ማለትም ካይዘን እና BSC የመሳሰሉትን ለመተግበር ያስችላል ብለዋል፡፡

በዚህ ውድድር በሚበዛበት ፣ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት በሚታይበት፣ የደንበኞች ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ተለዋዋጭ እና ምርቶችን በደንበኞች ፍላጎት ብቻ መስራት ግድ የሆነበት ጊዜ ነው፡፡ በመሆኑም ትርፋማነት  ለማስቀጠል በደንበኞችና አቅራቢዎች ዘንድ መተማመንን ለመፍጠር የአሰራር ማሻሻያዎች መከለስ እና መሻሻል የሚያስፈልጋቸውን አሰራርና ስርዓቶች ለመለየት፤ ለመተግበር እንዲሁም ተቋማት የላቀ ብቃት እንዲኖራቸው ቁልፍ ሚና ስላላቸው ሁላችንም በምንሰራው ስራ የአሰራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን መደበኛ የስራችን አካል መሆኑን ተረድተን በዚህ ልክ መስራት ይገባናል በማለት ቡድን መሪው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡