በሀገራችን ከ40% በላይ የማህጸን በር ካንሰር መስፋፋቱ በስልጠናው ተገልጿል፡፡
ህዳር 27ቀን 2017 ዓ.ም ዓለምአቀፍ የነጭ ሪቫን ቀንን ምክንያት በማድረግ በድርጅቱ ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ አገልግሎት ፅ/ቤት አዘጋጅነት ከጤና ተቋም በመጡ የጤና ባለሙያዎች ከድርጅቱ የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ ሴት ሰራተኞች በካንሰር ህመም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደተሰጠ መረዳት ተችሏል፡፡
አምራች የሆነው የድርጅቱ ማህበረሰብ በዘመናችን ካሉ የጤና ስጋቶች ራሱን ይጠብቅ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠሩ ተገቢ እንደሆነ የስርዓተ ፆታና ማህበራዊ አገልግሎት ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሃይማኖት ይገልፃሉ፡፡ የማህፀን ጫፍ ካንሰር አሁን ባለንበት ዘመን በተለይ በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ስልጠናውን በሰጡት የጤና ባለሙያ የተገለፀ ሲሆን የተሰሩ ጥናቶች እንደሚገልጹት ከ40% በላይ የሚሆኑ ሴቶች የማህጻን በር ካንሰር ተጠቂ ናቸው ተብሏል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር እንደሚችል የተናገሩት የጤና ባለሙያው አንዳንድ ጊዜ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ቅድመ ወሲብ በመፈጻም፣ አንዲት ሴት ከተለያዩ ወንዶች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት በመፈፀም፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ባልታወቀ ምክንያት እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ቫይረሱ በወንዶች ላይም የጉሮሮ ካንሰር ሆኖ ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ፕሮስትሬት ካንሰር በሰዎች ላይ ከ8-20 ዓመት ሳይታወቅ ሊቆይ ይችላል ያሉት ባለሙያው ሴቶች ላይ በማህጻን አካባቢ የደም መታየት፤ ሸንት ሲሸኑ ማቃጠል፤ ሽታ ያለው ፈሳሸ መፍሰስ ሸንትን ቶሎ አለመጨረስ ወይም የመንጠባጠብ ሁኔታ፤ ጀርባ ማቃጠል ምልክቶቹ ሲሆኑ ይህንን ምልክት ሲታይ በፍጥነት ወደ ህክምና መሄድ ተገቢ እንደሆነና አለዚያ ግን ቫይረሱ ከተሰራጨ ገዳይ መሆኑን ተገልጻል፡፡
ህክምናው በሁሉም የመንግስት የጤና ተቋማት በነጻ እየተሰጠ እንደሚገኝ በስልጠናው የተገለፀ ሲሆን ህክምናውም ቫይረሱ ካልተሰራጨ በ7 ቀን መድሃኒት ወይም በቀላል ቀዶ ጥገና ሊድን ይችላል ተብሏል፡፡ የዓለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን በዓለም ለ46ኛ በሃገራችን ለ22ኛ በድርጅታችን ለ8ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል፡፡