የሥራ ጉብኝቱ በድርጅቱ ምስጢራዊ ህትመት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ በሚቀርብለት ሪፖርት መሰረት የድርጅቱን አፈፃፀም ከመገምገምና ድርጅቱን ሊያሻግሩ የሚችሉ አቅጣጫዎችን ከማመላከት ባሻገር የድርጅቱ ወቅታዊ አቋምን ለመረዳት የሥራ ላይ ምልከታዎችን የማድረግ ባህል አለው፡፡ ሥራ አመራር ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቻው ምልከታዎች የድርጅቱን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ከመረዳት ባለፈ ለበርካታ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የድርጅቱ ህልውና ላይ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
ታህሳስ 08 ቀን 2017 ዓ.ም የተደረገውን የስራ ጉብኝት የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል የመሩት ሲሆን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡ በድርጅቱ ምስጢራዊ ህትመት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ባተኮረው ጉብኝት ላይ ድርጅቱ ከደንበኞች የተቀበላቸውን ስራዎች በጥራት አትሞ በሚፈለገው ጊዜ ለማድረስ በሚያስችል ቴክኖሎጂ በመደራጀት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡
የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴ በማስጎብኘት በስራ ክፍሉ ስለሚከናወኑ ተግባራት ገለፃ ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ ሲሆኑ ከስራ አመራር ቦርድ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥጠዋል፡፡