ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ሥራን በመደገፍ በተጠናከረ ሁኔታ የችግኝ ተከላ ሥራን ተግባራዊ እንደሚያደርግ የብርሃን ሠላም ማተሚያ ድርጅት ገለጸ፡፡

የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ለ16ኛ ጊዜ የተካሄደውን ዓመታዊ የችግኝ ተካላ ሥራ ዕሁድ ሰኔ 30/2011 ዓ.ም በድሬ ግድብ ማከናወኑን አስታወቀ፡፡

የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ከየስራ ክፍሉ የተውጣጡ ሠራተኞችና ከፊል አመራሮች በድሬ ግድብ የችግኝ ጣቢያ በመገኘት ከ2 ሺህ በላይ የሚሆን የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን መትከሉን ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ የሆኑት አቶ ሽታሁን ዋለ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የችግኝ ተከላ ሥራው በሀገር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተተገበረ ያለውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡ የችግኝ ተከላ ሥራው ለብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ትርጉም አለው ያሉት አቶ ሽታሁን ፤ ድርጅቱ የወረቀት ምርቶችን የሚያገኘው ከዛፍ እንደመሆኑ መጠን ለችግኝ ተከላ እና ደን እንክብካቤ ሥራ የሚንሰጠው ትኩረት በዚሁ የተቃኘ ነው ብለዋል፡፡

ችግኞችን መትከል ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተከታታይነት ያለው የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና እና ክትትል የማድረግ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል፡፡ አቶ ሽታሁን አያይዘውም ችግኞች ሲተከሉ በጥንቃቄ እና መጽደቅ በሚያስችል ሁኔታ መተከል እንዳለበትም ለችግኝ ተከላ ሥራ ለተገኙ የድርጅቱ ሠራተኞች ባስተላለፉት መልዕክት አሳስበዋል፡፡ በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ ከተገኙ ተሳታፊ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶች ስለ ችግኝ ተከላ ሥራ በሰጡት አስተየየት፤ ሀገራችን ለገጠማት የደን መመናመን አደጋን የሚቀርፍ በመሆኑ የችግኝ ተከላ ሥራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው  እየተሰራ ያለውም ተግባር የሚበረታታ፣ መልካም እንቅስቃሴ እና የሚደገፍም ነው ብለዋል፡፡