የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ

የድርጅቱን የ2014 በጀት ዓመት የኦፕሬሽንና የለውጥ ስራዎች ዕቅድ አፈፃፀም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል መሰብሰብያ አዳራሽ ተገመገመ፡፡ በግምገማው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ማሞ እስመለዓለም እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኦፕሬሽን፣ የለውጥ ስራዎች፣ የፋይናንስና የፕሮጀክት አፈፃጸም እንዲሁም በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት በድርጅቱ የዕቅድ ዝግጅት ፕሮጀክት ጥናትና ክትትል አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ መኮንን አበራ በኩል ቀርቧል::

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ውስጥ የኦፕሬሽን ፣የፋይናንስ ፣የፕሮጀክት/ኢንቨስትመንት ፣የሪፎርም ሥራዎች፣የኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ማህበራዊ ኃላፊነት እና ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች አፈፃፀሞች በተመለከተ ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የነበረውን አፈፃፀም ግምገማ ግብረ መልስ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር የሆኑት ቃልኪዳን አረጋ በኩል በዝርዝር ቀርቧል፡፡

ድርጅቱ ያጋጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቹን ተቋቁሞ ስራ ላይ መቆየቱና ችግሮቹን ለመፍታት የሚያደርጋቸው ጥረቶች፣ በምርት በሽያጭና በፋይናንስ አፈፃፀም ጠንካራ በመሆኑ ወደ ኢንቨስትመንትና ማስፋፋት ለመሸጋገር ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን በግብረ መልሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

ለአሮጌ ማሽኖች ተገቢ ጥገናዎችን በማድረግ የህትመቱ ሥራ እንዲቀጥል መደረጉ፣ ለግብዓት፣ መለዋወጫና ለተወሰኑ የህትመት ማሽኖች የውጭ ምንዛሪ ትኩረት በመስጠትና ክትትል በማድረግ ማስፈቀድ መቻሉ፣ አስፈላጊ ግብዓቶችንና መለዋወጫዎችን ማሟላት መቻል፣ የገቡ ሥራዎችን በወቅቱ ለማውጣት ሰራተኛውና ማኔጅመንቱ በትኩረትና በቅንጅት መስራቱ፣ የትርፍ ዕቅድን ማሳካት መቻሉ፣ ለዋና ዋና ደንበኞች ሥራዎች የማስረከቢያ ጊዜ ጠብቀው እንዲወጡ መደረጉ በበጀት ዓመቱ ድርጅቱ ካከናወናቸው ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን በግምገማው ተገልፀዋል፡፡

የ2013 በጀት ዓመት ሂሳብ በIFRS መሠረት ተመርምሮ በወቅቱ መዝጋት እና በውጭ ኦዲት ተመርምሮ ሪፖርት መቅረቡ እና የኦዲት አስተያየቱም ከስህተት የፀዳ መሆኑ በእቅድ አፈፃፀም ግብረ መልስ ላይ ተመላክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮርፖሬት ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት፣የውስጥ ኦዲት በዕቅዱ መሠረት የበጀት ዓመቱ የዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሞ መቅረቡ፣ የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ድርጅቱን መደገፉ፣ ድርጅቱ የስጋት ዓይነቶች እና መከላከያዎቹን በመለየት ለመስራት ጥረት መደረጉ እና የውስጥና የውጭ ኦዲት ግኝቶች መርሃ-ግብር በማዘጋጀት ለማስተካከል ጥረት መደረጉ በጠንካራ ጎን የተገመገሙ መሆናቸውን በሪፖርቱ ላይ ተገልፀዋል ፡፡

በድርጅቱ የሚገኙ ማምረቻ መሳሪያዎች በእርጅና ምክንያት በተደጋጋሚ በብልሽት መቆምና የባከኑ ሰዓቶች /Idle-time/ መጨመር፣ ለአዳዲስ ማሽኖች የውጭ ምንዛሪ ያለማግኘትና መግዛት ያለመቻል፣ የግንባታ ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ አለማጠናቀቅ፣ በቂ የመጽሃፍት ህትመት ያለማግኘት በአፈፃፀም የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን በግምገማው ተመላክቷል፡፡

የሚስጥራዊ ሰነዶችን ህትመትን በተመለከተ በሃገራችንና በአለም ላይ በፍጥነት እያደገ ያለ የቢዝነስ ዘርፍ ሲሆን የድርጅቱ ሽያጭ እና አገልግሎት በአዲስ ኢንቨስትመንት ወደ መስራት እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ መጽሃፍት ህትመትን በተመልከተ ድርጅቱ ከመንግስት ከሚያገኘው ስራ በተጨማሪ ከግል ድርጅቶች እና ከግለሰቦች ስራን የማግኘት እና የመስራት እንቅስቃሴ ማጠናከር፣ አብዛኛው የድርጅቱ ሃብት በኢንቨንተሪ እና በባንክ የተከማቸ በመሆኑ ይህን ሃብት ወደ ኢንቨስትመንት የሚቀየርበት መንገድ በማፈላለግ ለስራ ማስኬጃ በብድር መስራት የሚቻልበት መንገድ ቢፈለግ፣ ለእያአንዳንዱ ፕሮጀክት የትግበራ ፍኖተ ካርታ ቢያዘጋጅ እና ግልጽ የውጤታማነት መለኪያ KPI ቢኖር የሚሉ ጉዳዮች በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን በግብረ መልስ ሪፖርቱ ላይ ተገልፀዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ማሞ እስመለዓለም እንደተናገሩት ድርጅቱ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ የዓመቱን እቅድ አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ ማከናወኑን ገልፀው ለአፈፃፀመሙ ውጤታማነት የቦርዱ ፣የማኔጅመንቱና የሰራተኞች የተቀናጀ ስራ የጎላ ሚና እንደነበረው ገልፀዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አያይዘውም ድርጅቱ ሂሳቡን በIFRS መሠረት ተመርምሮ በወቅቱ መዝጋት እና በውጭ ኦዲት ተመርምሮ ሪፖርት መቅረቡ እና የኦዲት አስተያየቱም ከስህተት የፀዳ መሆኑ ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ መሆኑን ጠቅሰው ለቀጣይ ድርጅቱ ለሚያከናውነው ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንና ይህን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ድርጅቱ ያለውን ሀብት ኢንቨስት በማድረግ ስራዎችን በማስፋፋትና ተጨማሪ አዳዲስ ስራዎችን በመፍጠር ተጨማሪ ሀብት መፍጠር፣ድርጅቱ ከህትመት ጋር ያልተገናኙ ሌሎች ተጨማሪ ገቢዎችን የሚገኝበት ሁኔታ መፍጠር እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መስራት ለቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡

ድርጅቱ በዓመቱ ያስመዘገበውን ውጤት አበረታች መሆኑን የገለፁት አቶ ማሞ በቀጣይ በበጀት ዓመቱ የታዩትን ክፍተቶች በማስተካከል የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም ድርጅቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ያጋጠመውን የማምረቻ መሳርያዎች ግዥ ችግር ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ መስራቤታቸው ማንኛውም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡