ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከአፈፃፀም አንፃር ያገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ

የድርጅቱ የ2014 በጀት ዓመት እና የ2015 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም፣ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት እና ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡

ህዳር 10 ቀን 2015 በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው መርሃ ግብር የድርጅቱ ሥራ አመራር ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉልን ጨምሮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፣ የማኔጅመንት አባላት እና አጠቃላይ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

መርሃ ግብሩ በበጀት ዓመቱ በሞት የተለዩ የድርጅቱ ሠራተኞች በህሊና ፀሎት በማስታወስ የተጀመረ ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት እና በ2015 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ውስጥ ከዕቅድ አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እንዲሁም በ2014 በጀት ዓመት ከሠራተኞች ጋር በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ከመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተነሱ ችግሮች የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች አፈጻጸም በድርጅቱ ዕቅድ ዝግጅት፣ ፕሮጀክት ጥናትና ክትትል አገልግሎት ኃላፊ አቶ መኮንን አበራ ቀርቧል፡፡

በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው ድርጅቱ በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ በምርት፣ በሽያጭና በትርፍ ከዕቅድ በላይ እንደተከናወነና በተመሳሳይ በ2015 በጀት ዓመት ይህንኑ ለማስቀጠል የሚያስችል ጅማሮ መኖሩ በአንደኛ ሩብ ዓመት በተመዘገበው አፈፃፀም ታይቷል፡፡

በተያያዘም ስራዎችን በወቅቱ አጠናቆ በማውጣት በኩል ማምረቻ መሳሪያዎችን ከውጭ ባለሞያ በማስመጣት ጭምር ተጠግነው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ዋና ዋና ግብዓቶችን ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ በመግዛት ለማሟላት በተደረገ ጥረት፤ አጠቃላይ የድርጅቱ ሰራተኞችም ከስራ ሰዓት ውጭ ጭምር 24 ሰዓት በመስራት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት፤ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት እንደተቻለ መረዳት ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2014 በጀት ዓመት ከሠራተኞች ጋር በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ከመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተነሱ ችግሮች የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ተግባራትና አሁን ያሉበት ደረጃ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በዕለቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተሳታፊ ሰራተኞች ለተነሳው ጥያቄና አስተያየት በድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንዲሁም በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሰራተኞች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የ2014 በጀት ዓመት አፈጻፀም በጋራ በተደረገ ጥረት ማሳካት መቻሉን፣በተመሳሳይ መልኩ የ2015 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ አመት አፈፃፀምም የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የጋራ ጥረት በመደረጉና ሠራተኛው ሥራ ላይ አተኩሮ በመስራቱ ከዕቅድ በላይ እንደተፈፀመና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል በበኩላቸው 100 ዓመታትን እንደተሻገረ ድርጅት ዓለም በህትመቱ ዘርፍ የደረሰበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሊሆን እንደሚገባና ይህንንም ለማድረግ በሰው ኃይል ልማት ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ እንዲሁም ዘመናዊ መሳሪያዎችን ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሰብሳቢው አክለውም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ህትመት ሥራን ምስጢራዊነቱን በጠበቀ መልኩ በመሥራትና በጊዜ በማድረስ ረገድ ለተሰራው የተሳካ ሥራ የድርጅቱን አመራርና አጠቃላይ ሠራተኞችን አመስግነው ከአፈፃፀም አንፃር የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ድርጅቱ ሰላሙ የተጠበቀ ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በበዓል አከባበሩ ላይ በድርጅቱ ሲያገለግሉ ቆይተው በጡረታ ለተሰናበቱና በቅርቡ በጡረታ ለሚሰናበቱ ሠራተኞች የእውቅና ሽልማትና ሠርተፊኬት ተሰጥቷል፡፡