የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተገመገመ፡፡
ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት አበረታች ውጤት አስመዝግቧል፡፡
የካቲት 07 ቀን 2016 ዓ.ም ስካይ ላይት ሆቴል በተደረገው ግምገማ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ አብዱረህማን ዒድ ጣሂር እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድና ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡
በግምገማ መርሃ ግብሩ ላይ የድርጅቱ የኦፕሬሽን፣የፋይናንስ፣የሪፎርም፣ኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ የፕሮጀክት፣ኦዲትና IFRS እና ማህበራዊና አካባቢያዊ ግዴታዎች አፈፃጸም እንዲሁም በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት በድርጅቱ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዳይሬክተር በሆኑት አቶ መኮንን አበራ በኩል ቀርቧል::
ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ የኦፕሬሽን ፣የፋይናንስ ፣የፕሮጀክት/ኢንቨስትመንት ፣የሪፎርም ሥራዎች እና የኮርፖሬት ገቨርናንስ አፈፃፀሞች በተመለከተ የነበረውን አፈፃፀም ግምገማ ግብረ መልስ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አስማ ረዲ በኩል በዝርዝር ቀርቧል፡፡
የአፈፃፀም ሪፖርቱ በድርጅቱ ማኔጅመንት በዝርዝር ውይይት ተደርጎበት ለሥራ አመራር የቀረበና አስፈላጊውን መረጃ ያካተተና እንዲሁም በሪፖርቱ ያልታዩ ጉዳዮች ላይ በማኔጅመንቱ በኩል በቂ መረጃዎች መቅረባቸውን በግምገማው ተገልጿል።
በግማሽ ዓመቱ ውስጥ የተመረተው የምርት መጠን ከእቅድ በላይ በመሆኑ መልካም አፈጻጸም ሲሆን በግማሽ ዓመቱ ለማምረት የታቀደው የምርት መጠን 81,474,590 ካሬ ሜትር እንደሆነና የተመረተው ምርት በመጠን 95,968,552 ካሬ ሜትር በመሆኑ አፈጻጸሙ ከእቅድ በ17.78% በልጦ መከናወሁ ተመላክቷል፡፡
በተያያዘም ድርጅቱ በምርት ሽያጭ ብር 742,386,000 ገቢ ያገኘ ሲሆን አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንጻር 112.39% መሆኑ ተጠቅሷል በሌላ በኩል ከህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ እንዲሁም ከአሳታሚነት ሥራ ብር 5,563,000 የተገኘ ሲሆን 99.2 በመቶ አፈጻጸም መኖሩ መልካም አፈጻጸም ነው ተብሏል።
ድርጅቱ በግማሽ ዓመት ውስጥ ያገኛል ተብሎ የታቀደው ትርፍ ከታክስ በፊት ብር 215,595,031 ሲሆን ብር 233,739,963 ለማትረፍ በመቻሉ አፈጻጸሙ 108.42 በመቶ ሲሆን ከዕቅዱ በብር 18,144,932 ወይም በ8.42% ከፍ ብሎ ተከናውኗል ተብሏል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱና ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቁና አስተያየቶች የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድና ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ አብዱረህማን ዒድ ጣሂር በግምገማው ማጠቃለያ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተመዘገበው አፈፃፀም ጥሩ መሆኑን ገልፀው፣ ድርጅቱ በአፈፃፀምና እቅዱ ላይ በየደረጃው ካሉ አመራርና ሰራተኞች ጋር ውይይት ማድረጉ የጋራ ግንዛቤ ከመፍጠርና ለተፈፃሚነቱ በጋራ ከመረባረብ አንፃር የጎላ ሚና እንደሚኖረውና ይህም ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል፤ የድርጅቱ የውስጥ ኦዲት ሥራዎች ግልፅ አሰራርን ከማስፈን ባሻገር የውጪ ኦዲትን ሥራ ሊያግዝ በሚችል መልኩ መከናወኑ፤ የድርጅቱ ዕቅድ የገበያውን ሁኔታ በሚገባ ባጤነ መልኩ መዘጋጀት መቻሉ፤ በምስጢራዊ ህትመት አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ሥራ እንዲሁም የደንበቦች ቅሬታ ለመፍታት የሚደረገው ጥረትን አድንቀዋል፡፡
አክለውም ድርጅቱ ከመንግስት ከሚያገኘው ሥራ በተጨማሪ ከግል ድርጅቶች እና ከግለሰቦች ስራን የማግኘት እና የመስራት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባና ከዲጂታል ፈተና ህትመት ጋር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡