ድርጅቱ በብሔራዊ ቤተ-መንግስት በተሄደው የእውቅና እና ሽልማት ሥነ-ስርዓት ሽልማቱን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተረክቧል፡፡
አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በህትመትና ተጓዳኝ አገልግሎቶቹ ለትምህርት መስፋፋት፣ ለወቅታዊ መረጃዎች ስርጭት እና ሌሎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መቀላጠፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ለብዙሃን ተደራሽ የሆነው ድርጅት የሚጠበቅበትን መንግስታዊ ግዴታዎችን በአግባቡ በማከናወንም መልካም ስምን ገንብቷል፡፡

መስከረም 30 ቀን/2017 ዓ.ም በተካሄደው የ6ኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት ሥነ-ስርዓት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሲካሄድ 550 ግብር ከፋዮች በፕላቲንይም በወርቅነና በነሀስ ደረጃ እውቅና እና ሽልማት ያገኙ ሲሆን ግብር ከፋዮች በሀገር ውስጥ ገቢ በ12 እና በጉምሩክ በ7 የመምረጫ መስፈርቶች መሰረት ተመዝነው እውቅና የተሰጣቸው መሆኑን በገቢዎች ሚኒስቴር ተገልጿል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በወርቅ እውቅና ከተሰጣቸው ግብር ከፋዮች መካከል አንዱ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሲሆን ግብር ለአንድ ሀገር አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው እድገት አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ላከናወኑት ግዴታን የመወጣት ተግባር ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በመድረኩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እጅ የድርጅታችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡
ድርጅታችን የመንግስት ግዴታዎችን በወቅቱና በአግባቡ በመፈፀም ታማኝነቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡