ብርሃንና ሰላም የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በቪዲዮ ኤዲቲንግና አኒሜሽን ሙያ አዲስ የስልጠና ፕሮግራም ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገለፀ

ኮሌጁ ለሶስተኛ ጊዜ በደረጃ ሶስት የህትመትና ግራፊክስ አርት ሙያ ያሰለጠናቸውን 51 ተማሪዎች በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመርቋል፡፡

ጥቅምት 02 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የመረቃ በዓል የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፤ የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን ካሳ፤የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት፤የኮሌጁ አስተዳደር ሠራተኞች እና አሰልጣኞች፤ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ተገንተዋል፡፡

በምረቃ በዓሉ ላይ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን ካሳ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በህትመት ኢንዱስትሪ የሙያ መስክ በሀገር ደረጃ ጎልቶ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም ሙያዊ የህትመት ቴክኖሎጂ ክፍተቶች በስልጠና መፍትሄ እንደሚያገኙ በማመን፤ እንዲሁም ባካበተው የበርካታ አስርተ አመታት የህትመት ሥራ ልምድ እና ባለው አደረጃጀት ላይ በመመስረት በ2007 ዓ.ም የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በማቋቋም ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል፡፡

ኮሌጁ የስልጠና ትኩረቱን በህትመት ዘርፍ ላይ ብቻ በማድረግ በ2010 ዓ.ም የማሰልጠን እውቅና ፍቃድ ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ማግኘቱን የገለፁት አቶ መስፍን በሀገር ደረጃ ለዘርፉ በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ እና ሥርዓተ ትምህርት መሰረት ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችለውን የሥልጠና ወርክሾፖችና ግብዓት በማደራጀትና በማሟላት በህትመትና ግራፊክ አርት ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሶስት በማሰልጠንና በማስተማር ረገድ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

አክለውም ነባራዊውን የህትመት ቴክኖሎጂ የገበያ ፍላጎት መሰረት በማድረግ በቀረጻቸው የአጫጭር ጊዜ ሥልጠናዎች አማካኝነት በህትመት ቴክኖሎጂ፣ በግራፊክ ዲዛይንና አርት፣ በህትመት ዋጋ ትመና እና በሲልክ ስክሪን የህትመት ሙያ ዘርፎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች ተቀብሎ በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረግ የቻለ ሲሆን በተያዘው ዓመት  በቪዲዮ ኤዲቲንግና አኒሜሽን ሙያ አዲስ የስልጠና ፕሮግራም ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል፡፡

እንደ ዲኑ ገለፃ ከማሰልጠንና ከማስተማር ሂደቱ ጎን ለጎን ኮሌጁ ለህትመት ድርጅቶችና ለዩኒቨርሲቲዎች በህትመት ቴክኖሎጂ ዙሪያ የማማከርና የህትመት ማሽን ጥገና አገልግሎት በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝና በማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ከተለያዩ ድርጅቶች የተላኩ ባለሙያዎችንና የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች በህትመት እና በግራፊክ ዲዛይንና አርት ከክፍያ ነጻ ሰልጠና ሰጥቷል ብለዋል፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ በበኩላቸው ህትመትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን እንዲቻል እና በህትመት ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍትት ለመሙላት ይቻል ዘንድ የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በመክፈት ለ3ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ማስመረቁንና ለሀገራችን ህትመት ዘርፍ የተሻለ አቅም ሊፈጥር የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሂደት ውስጥ ኮሌጁ እየተጋ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተመራቂዎች ከሥራ ጠባቂነት መንፈስ በመውጣት የራስን ሥራ በመፍጠር የተሻለ ገቢ በማግኘት ራስንና ሀገርን መጥቀም የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ያገኛችሁበት የተከበረ ሙያ መሆኑን በመገንዘብ ሀገራችን እያስመዘገበች ያለችውን ዕድገትና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡