የማህብራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት በትኩረት እንደሚሰራ የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ገለጸ፡፡

የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የሚጠበቅበትን የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ በዕቅድ ይዞ ለተግባዊነቱም በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡

በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የኢንዱስትሪና ሠራተኞች ደህንነት እና ጤንነት አጠባበቅ ቡድን መሪ የሆኑት ሲስተር አበባዬ መርዕድ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ የማህበራዊ ኃፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት አኳያ ሥራውን የሚያንቀሳቅስ ኮሚቴ በማዋቀር በዕቅድ የሚመራ ተግባራትን በመለየትና በጀት በማዘጋጀት ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው የእንቅስቃሴውን አፈጻጸም ክትትልና ግምገማ በማድረግ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሠላም  ለማስቀጠል እንዲሁም የአካባቢ ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ የክትትል ሥራው በተገቢው ሁኔታ እየተመራ ይገኛልም ብለዋል ሲስተር አበባዬ፡፡

ድርጅቱ በማህበራዊ አገልግሎቱ ይበልጥ ተደራሽ የሚያደርጋቸው የማህበረሰብ ክፍል እንዳሉ የጠቆሙት ሲስተር አበባዬ ወላጆጃቸውን በኤች አይቪ ኤድስ ምክንያት በሞት ያጡ ህጻናት፣ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ስራ አጥ ወጣቶች እንዲሁም በጫማ ማስዋብ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ ተደራሽ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ የማህበራዊ አገልግሎት ሥራውን በዕቅድ አካቶ ከሚተገብራቸው በተጨማሪ ከግለሰቦች ወይም ከተቋማት በሚቀርብ ጥያቄ ተቀብሎና አሳማኝነቱን አረጋግጦ ድጋፍ ያደርጋልም ብሏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጅቱ በ2010 ዓ/ም በእቅድ ይዞ የአገልግሎት ሥራውን ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ሲሰተር አበባዬ በጥሬ ገንዘብ ከ380 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለድጋፍ አገልግሎት ሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን ለተለያዩ ወረዳዎች የግንባታ ድጋፍ ማድረጉንም ቡድን መሪዋ ገልጸዋል፡፡ በ2010 ዓ/ም ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራት በተመሳሳይ መልኩ በ2011 በጀት ዓመት ለመፈጸም አገልግሎቶቹ ተለይተው በዕቅድ ተይዘው ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እንዳለ ገልጸው ሥራውን የሚከታተል ኮሚቴ ተግባራቶቹን የጋራ በማድረግና በማናበብ ተግባራዊ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ የበለጠ እና የተሻለ ስራን ለመስራት በልዩ ትኩረት እንዲሰራ የጠየቁት ሲስተር አበባዬ፤ ድርጅቱ የተጣለበትን የማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ብሎም ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሠላም ለማስፈን እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በቀጣይም በይበልጥ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡