የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በዘርፉ እስከ አሁን ባለው አፈጻጸም የታዩ ጉድለቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጥናቶችንና የገበያ መስፋፊያ ስልቶችን በመጠቀም ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ጠንክረው በመስራት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡
በ
ድርጅቱ የገበያ ጥናትና ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ፍጹም ወረደ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በገበያ ውስጥ ያለውን ድርሻ በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ ሁኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡ በእስከ አሁኑ ስራ በገበያ ልማት ዙሪያ ከ5 በላይ ጥናቶች የተሰሩ ሲሆን ይህም የድርጅቱን የገበያ ማስፋፊያ ሥራዎችን ከመስራት አኳያ እና ወደ ውጭ ሀገራት እየወጡ የሚታተሙ ህትመቶችን በሀገር ውስጥ እንዲታተሙ የሚያስችል አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ለህትመት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት እና የውጭ ምንዛሪው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲውል የሚያደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ፍጹም አያይዘው ገልጸዋል፡፡ የማተሚያ ድርጅቱ የደንበኞችን ፍላጎት ሟሟላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡ የደንበኛ እርካታን ከሟሟላት አኳያ ሥራዎች በትኩረት እየተተገበሩ ነው ያሉት አቶ ፍጹም፤ የደንበኞችን እርካታ ደረጃ ዳሰሳ በጥናት መለየት፣ በደንበኞች በኩል የሚነሱ አስተያየትና ቅሬታ መረጃዎች እንዲደራጅ በማድረግ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ እና ሌላ ተዛማጅ ስራዎችን በመተግበር እርካታቸው እውን እንዲሆን ይሰራልም ብሏል፡፡ የ2010 የገበያ ጥናት እና ልማት የጥናቱ ውጤት መረጃ እንደሚያመለክት የደንበኞች እርካታ 77 % አከባቢ ሲሆን ውጤቱ የሚያመለክተውም በስታንዳርዱ መሰረት የደንበኞች እርካታ ላይ ገና መሰራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች እንዳሉ ይጠቁማል፡፡ ድርጅቱ በቀጣይ የደንበኞችን እርካታ እውን ከማድረግና ትርፋማነቱን ጠብቆ ከመሄድ አንጻር መሰራት የሚገባቸውን ነጥቦች የለየ ሲሆን፤ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት፣ የማስረከቢያ ጊዜን ጠብቆ ምርቶችን ለደንበኞች ማስረከብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ የክምችት መጠንን ማሳደግ፣ ባለሙያዎችን ማብቃት እና ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለበት ጥናቱ ያመላክታል፡፡
ድርጅቱ ተወዳዳሪነቱን ጠብቀው እንዲቀጥል የድርጅቱን ምርትና አገልግሎት የማስተዋወቅ ሥራ በተደራጀ መልኩ እንደሚሰራ የጠቆሙት ቡድን መሪው፣ የህትመት ውጤቶችንና የተለያዩ ብዙሃን መገናኛ ሚዲያዎችን በመጠቀም እንዲሁም በኤግዝብሽንና ባዛር መድረኮች ላይ በመሳተፍ የድርጅቱ ምርትና አገልግሎት ለመረጃ ፈላጊዎችና ለደንበኞች የሚተዋወቅበትን አሰራር እንደሚጠቀም አቶ ፍጹም ገልጸዋል፡፡ በዚህም የደንበኞችን መረጃ በመከታተል የድርጅቱ ገቢ እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአታሚ ደንበኞች የሥራ እንቅስቃሴ መረጃ የገበያ ድርሻው ያለበትን ሁኔታ ለግብዓትነት ይቀርባልም ብለዋል አቶ ፍጹም፡፡