የገቢዎች ሚኒስቴር ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በደረሰኞች ላይ ልዩ መለያ ኮድ (QR-Code) አካቶ ማተም በሚያስችል አሠራር ዙሪያ የመግባቢያ ስነድ ተፈራረመ

የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ሥነ-ስርዓት በገቢዎች ሚኒስቴር እና በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት መካከል በዛሬው ዕለት የተካሄደ ሲሆን ዓላማውም ከታክስ ደረሰኝ ህትመት ጋር በተያያዘ ልዩ መለያ ኮድ (QR-Code) ተካቶ ማተም፤ የህትመት ጥያቄ መቀበል፣ ከታተመ በኋላ የስርጭት እና የቁጥጥር ሥርዓትን ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ማስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የገቢዎች ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት  ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደ ሀገር ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ገቢን በብቃት መሰብስብ እና ሀገራዊ ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሽፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ለግብር ከፋዩ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት የማንዋል ደረሰኝ አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም የሀሰተኛ ደረሰኝ ህትመት መበራከት በግብር አሰባበሰቡ ላይ ፈተና ሆኖ ስለመቆየቱ ተገልጿል፡፡ የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደርን ለማሻሻል የወጣ መመሪያ ቁጥር 188/2017ን አጽድቆ ስራ ላይ በማዋል ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ እያንዳንዱ የደረሰኝ ቅጠል ሲታተም ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) ተካቶ እንዲመታተም እና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በህትመት ዘርፉ ፈርቀዳጅ የሆነና የአንድ መቶ አራት ዓመት ልምድ ካለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በጋር ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ አያይዘውም ደረሰኝ እንዲታተም ፍቃድ ከመስጥት ጀምሮ ያሉ አገልግሎቶችን ማስተናገድ እንዲቻል የራሱ የሆነ ዲጂታል ፕላትፎርም የተዘጋጀ ስለሆነ ደረሰኝ የሚያሳትም ማንኛውም ግብር ከፋይ በዚሁ መንገድ መስተናገድ የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡በተጨማሪም የማንዋል ደረሰኝ ተጠቃሚ የሆኑ ግብር ከፋዮች ከታህሳስ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ የማንዋል ደረሰኝ የማሳተም ጥያቄያቸውን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን አመላክተው ከየካቲት 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብቻ የታተም የማንዋል ደረሰኝ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው የገቢዎች ሚኒስቴር የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣት እንዲችል በተለይም ከገቢ አሰባስቡ ጋር በተገናኛ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እንዲቻል ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በጋራ እንዲሰራ በመመረጡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ድርጅቱ ሚስጥራዊ ህትመቶችን በማተም ካለው የስልሳ ዓመታት ልምድ በመነሳት ደረጃውን የጠበቀ፣ ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) የተካተተበት እና አስመስሎ መስራት በማይቻል መልኩ የህትመት ሥራውን ለማከናወን በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም ግብር ከፋዮች ለገቢዎች ሚኒስቴር በሚያቀርቡት የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ መሠረት የሚቀርቡ የህትመት ትዕዛዞችን ተቀብሎ ደረሰኞችን ለማተም በቂ ዝግጅት ስለመደረጉ ገልጸው ድርጅቱም ይህን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በተገባው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሰረት ለተግባራዊነቱ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡-የገቢዎች ሚኒስቴር ፌስ ቡክ ገፅ