ከህዝብ ክንፉ ጋር የተደረገ ውይይት

ድርጅታችን ከተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የህዝብ ክንፍ በማዋቀር የድርጅቱን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ፣ የእቅድ አፈፃጸምና የአምስት አመቱን ስትራቴጂክ እቅድ ላይ በ10/06/08 ዓ.ም በፍልውሃ አገልግሎት ፊንፊኔ አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተካ አባዲ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ድርጅቱ ከህዝብ ክንፉ ጋር በጋራ መሆን ያቀዳቸውን ለማከናወናን እና ለሚያጋጥሙን ችግሮችም የመፍትሔ አጋር በመሆን በየኔነት ስሜት ያግዘናል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ጊዜ በየወቅቱ ግንኙነትን በማጠናከር አብራችሁን እንደምትሰሩ ሙሉ እምነታችን ነው፤ ድርጅቱም የተሻለ ሥራ ለመስራት ዝግጁ ነው፤ ስለዚህ ጥምረቱ ወደፊት የተጠናከረ የህትመት ኢንዱስትሪ ለመገንባትና በሃገሪቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ የህትመት ተቋም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

በዕለቱም የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በድርጅቱ የድጋፍ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ መለሰ ስሜነህ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ እንደ አቶ መለሰ ስሜነህ ገለፃ በቀጣይ አምስት ዓመታት ድርጅቱ አምስት ዋና ዋና ዘርፎችን በተቋም ደረጃ በማዋቀር ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬት የሚያድግበትን ሁኔታ ለማከናወን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡ አምስቱ ዋነ ዋና ዘርፎችም የመደበኛ ህትመት፣ የሚስጥራዊ ህትመት፣ የህትመት ቴክኖሎጂ አካዳሚ፣ የአሳታሚ እና የፓኬጂንግ/ህትመት ወረቀቶችን የማምረት/ ናቸው ብለዋል፡፡

በድርጅቱ የህትመት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ የ2008 በጀት ዓመት ዕቅድ እና ያለፈውን አፈፃጸም ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ አቅርበዋል፡፡ ያለፈው አፈፃጸም አበረታች መሆኑን እንዲሁም ያጋጠሙትን ችግሮች እና የተወሰዱትን መፍትሔዎች በቀጣይም በጋራ ለምናደርገው ውይይትና ስራዎች በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡ ከቀረቡት ሰነዶችም በመነሳት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች የተሰጠ ሲሆን አንዳንድ ተሳታፊዎች የታቀዱት ተግባራት ለሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አስፈላጊና በቀጣይ ድርጅቱ ጠንክሮ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡