የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስፍን ካሳ እንደገለጹት፤ ሰፊ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ያለው የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጁ፣ የተያዙ የስልጠና መርሃ ግብሮቹን በተደራጀ እና በተጠናከረ መልኩ ለመስጠት በሙሉ አቅምና ዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡ ኮሌጁ እውቅና ባገኘባቸው የሙያ ስልጠና መስክ ላለፉት 2 ዓመታትና ከዚያም በላይ ሰልጣኞችን ተቀብሎ እያሰለጠነ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በ2012 ዓ.ም የፌደራል የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በተላከው የ2012 የትምህርት ዘመን ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት መግቢያ መቁረጫ ነጥብ መሠረት ተማሪዎቹን ተቀብሎ ለማሰልጠን በቂ ዝግጅት አድርጓዋል ብለዋል፡፡ የህትመት ኢንዱስትሪውን አንድ ደረጃ ወደ ፊት እንዲራመድ የህትመት ቴክኖሎጂው የበኩሉን ድርሻ የሚጫወት እና የላቀ ሚና አለው ያሉት አቶ መስፍን በዘርፉ የተማረ እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የህትመት ስራ መስራት የህትመት ጥራትን የበለጠ ያሻሽላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ የህትመት ኮሌጁ በእስከ አሁኑ የማሰልጠን ሥራው የድርጅቱን ሠራተኞች ጨምሮ ከ500 በላይ ሰልጣኞችን በአጫጭር ስልጠና አሰልጥኖ ወደ ገበያ የቀላቀለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መስፍን በያዝነው በጀት ዓመት በህትመት ዘርፍ አጫጭር ስልጠና እና ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት በህትመትና ግራፊክስ አርት ሙያ የማሰልጠን ፍቃድ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ኮሌጁ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርና ሀገራዊ ኃላፊነትን በተገቢው መልኩ መወጣት ወደሚቻልበት ሁኔታ እንዲደረስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ አቶ መስፍን አያይዘውም በ2012 ዓ.ም በአጫጭር ስልጠና በህትመት ቴክኖሎጂ (ክወና) ፣ በግራፊክ ዲዛይን እና በህትመት ዋጋ ትመና ዘርፎች ስልጠና እንዲሁም በህትመትና ግራፊክ አርት ከደረጃ I እስከ ደረጃ III ስልጠና ለመስጠትም ዝግጅቱን አጠናቆ በምዝገባ ላይ ነውም ተብለዋል፡፡ ሌሎች የስልጠና ዘርፎችን በቀጣይ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ላይ ያለ መሆኑም ታውቋል፡፡ ኮሌጁ በተቋማት ፍላጎት መሰረት (tailor training) ስልጠና አዘጋጅቶ ይሰጣለም ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ኮሌጁ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ማዕከል በህትመት ዘርፍ የሙያ ብቃት ምዘና (COC) ጣቢያነት ተመርጦ የምዘና ጣቢያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡