በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች ድጋፍ ተደረገ

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ነዋሪዎች ሃምሳ ሺህ ብር የሚገመት የተለያዩ የምግብ ፍጆታ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ፡፡

የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ዜጎች ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ተፅዕኖ ለመቆጣጠር እንዲቻል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ለመስራት መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሰረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች እንዲውል ታሳቢ የተደረገ ደጋፍ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም ተከናውኗል፡፡
የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ኃይለ ድርጅቱ ኮሮና ቫይረስ በሀገር፤ በድርጅቱም ሆነ በሰራተኞች ህልውና ላይ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጫና በመረዳት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወርዱ መመሪያዎችን በማስፈፀም እና ሌሎች በሽታን ለመቆጣጠር የሚያችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የምርት ሥራው ሳይቆም በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በጥንቃቄ እንዲተገበሩ የተለያዩ የመከላከያ ሥርዓቶችን በመዘርጋት ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለፁት ዳይሬክተሩ ማህበራዊ ግዴታዉንም ለመወጣት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ግምቱ ሃምሳ ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ዘይት፣ማካሮኒ፣ፓስታ፣ሩዝ፣የስንዴ ዱቄትና ሳሙና ያበረከተ ሲሆን በርክክብ ስነሥርዓቱ ወቅት ድርጅቱ ዋና ተልዕኮው ከሆነው የህትመት ስራ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በእንዲህ ያሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ተገቢና ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን ወገናዊነት የሚያሳይ ተግባር እንደሆነ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ኃይለ ገልፀዋል፡፡

ወረዳውን በመወከል የምግብ ፍጆታ ዕቃዎቹን የተረከቡት የወረዳው ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የትምህርት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ተፈራ ማሞ በበኩላቸው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ወረዳው ለሚያቀርበው የማህበራዊ ድጋፍ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ቀዳሚ መሆኑን ገልጸው የተደረገላቸውን ድጋፍም በወረዳው ሥም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ይህ ድጋፍና መልካም ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል፡፡