የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለድርጅቱ ማኔጅመንት አባላትና  መካከለኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጡ

የማኔጅመንት አባላትና መካከለኛ አመራሮች በሥራ አመራር ቦርድ የተሰጣቸውን ሥልጠና በውጤት ሊያሳዩት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

 በሀገራችን የህትመት ኢንደስትሪ ፈር ቀዳጅ የሆነው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ያለውን ክብርና ዝና አስጠብቆ ለማስቀጠልና በዘርፉ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጎልበት በዘመናዊ ማተሚያ መሳሪያና እና በሰለጠነ የሰው ኃይል ማደራጅቱ ወሳኝ እንደሆነው ሁሉ ድርጅቱን በመምራት ላይ ያሉ የማኔጅመንት አባላት የድርጅቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግሩት ዘንድ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል፡፡

ድርጅቱ በየበጀት ዓመቱ በዕቅድ አካቶ ለሰራተኞችና አመራሮች ከሚሰጠው ስልጠናዎች ባሻገር በሥራ አመራር ቦርዱ ተነሳሽነት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተዘጋጀው ሥልጠና የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚን ጨምሮ ምክትትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፤ የማኔጅመንት አባላትና ቡድን መሪዎች የተሳተፉበት እንደነበር መረዳት ተችሏል፡፡

በሥልጠናው የመክፈቻ ንግግር  ያደረጉት  የድርጅቱ ዋና ሥራ ስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ  የሥራ አመራር ቦርድ አባላቱ በራሳቸው ተነሳሽነት በትምህርትና በሥራ ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ለማካፈል ስልጠናውን በመስጠታቸው አመስግነው ድርጅቱ አሁን ባለው የገበያ ውድድር በተለመደው አሰራር ትርፋማና ውጤታዋ ሆኖ  መቀጠል ስለማይቻል  ድርጅቱን በዘመናዊ መሣሪያዎችና አሰራር ሥርዓቶች ከማደረጀት ጎን ለጎን የማኔጅመንቱንና የሰራተኛውን አቅም ማሳደግ ወሳኛ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው ይህንንና መሰል መርሃ-ግብሮችን በማዘጋጀት አመራሩ የተሻለ ግንዛቤ ኖሮት ድርጅቱን በተሻለ አግባብ መምራት እንዲችል ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ስልጠናውን ያስተባበረው የድርጅቱ የሰው ሀብት ልማት ቡደን መሪ አቶ ታመነ ዘውዱ ለአራት ቀናት ማለትም ታህሳስ 9፣10፣16እና 17/2013 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል  በተዘጋጀው ሥልጠና ሰባት የሥራ አመራ ቦርድ አባላት መሳተፋቸውን ገልፀው፤ የአመላካከት ለውጥ ፓራዳይም ሺፍት በስነ ምግባር ለታነፀ አመራርና ምርታማነት   በአቶ ጌታቸው በለጠ ፤ ሰነ ምግባር በአቶ ግርማ ወርቁ ፤ ማርኬቲንግና ቼንጅ ማኔጅመንት በአቶ ከፍያለው ብርሃኑ፤ ፈጠራ (innovation) በአቶ አማረ አሰፋ፤ ሊደርሺና ኮሙዩኒኬሽን በዶ/ር አበባ በየነ፤ sustainable and resource efficient production በዶ/ር ለማ ደንደና እና ግዢና ንብረት አስተዳደርና ፋይናንስ በወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የተሰጡ ስልጠናዎች እንደነበሩ  አስታውሰው  ስልጠናዎቹ የአመለካከት ለውጥ ከማምጣትና ድርጅቱን ወደተሻለ ደረጃ ከማሸጋገር አንፃር ከፍተኛ ሚና እንሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ቡድን መሪው አያይዘውም በቀጣይ በተለያዩ አዳዲስ ርዕሰ ጉዳዮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለአመራሩና ለሰራተኛው እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡

በሥልጠናው ታሳታፊ የነበሩት የድርጅቱ ድጋፍ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በላይ ኪዳኑ በበኩላቸው የሥራ አመራር ቦርድ አባላቱ የ2012 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ለድርጅቱ አመራር ሥልጠና በመሥጠት ድርጅቱን ከመምራት ባሻገር በተለያየ መስክ ያካበቱትን እውቀት ፣ልምድና ተሞክሮ በማጋራት የድርጅቱ ሥኬት አካል መሆን እንደሚፈልጉ ባሳወቁት መሰረት የሥልጠና መርሃ-ግብር ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም በሀገራችን በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት እንዲቆይ ተደርጎ አሁን ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ በላይ ገለፃ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ከተለያየ የሥራ መስክ እንደመሰባሰባቸው ለድርጅቱ አመራሮች የሚሰጡት ሥልጠና ለድርጅቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚኖረው ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ በድርጅቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሄው አካል ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ አቶ በላይ አክለውም በሌሎች የመንግስት ልማት ድርጅቶች አምብዛም ባልተለመደ መልኩ የሥራ አመራር ቦርዱ በራሱ ተነሳሽነት  የሰጠው ሥልጠና  በተጨባጭ የድርጅቱን አሁናዊ ሁኔታ ለመፈተሸና የማሻሻያ ሥራዎችን ለመተግበር የሚያስችል እደሆነ ጠቁመው ድርጅቱን በቅርበት በመከታተል ድጋፍ  በማድረግ ላለው የሥራ አመራር ቦርዱ አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በስልጠናው መጨረሻ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ  አቶ ሽታሁን ዋለ ግዜያቸውን ሰውተው በቂ ዝግጅት በማድርግ ለድርጅቱ በሚጠቅም መልኩ ስልጠናውን ለሰጡት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበው የማኔጅመንት አባላት በሥራ አመራር ቦርድ የተሰጣቸውን ሥልጠና በውጤት ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡