የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አመራሮች ውጤታማ የአመራር ሥነ-ምግባርን ተግባራዊ በማድረግ የድርጅቱን ራዕይ ዕውን ሊያደርግ የሚያስችል የተሻለ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
በድርጅቱ የስነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እያደገ የመጣውን የህዝብ የአገልግሎት ጥራት እና ስፋት ጥያቄ ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑ እና ህዝብን ማገልገል ስራቸው አድርገው የተቀበሉ አመራሮችን ለመፍጠር፤ስራቸውን በታማኝነት፤ በግልጽነት እና በተጠያቂነት መፈጸም የሚችሉ አመራሮች ለመፍጠር፤በየደረጃው ያሉ አመራሮች ማንኛውንም ሃላፊነት በሚመሩት ሰራተኛ እና በሚያገለግሉት ህዝብ ፊት በአርአያነት ሊጠቀስ በሚችል ደረጃ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ሲሆን መጋቢት 08/2013 ዓ.ም በድርጅቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡
የድርጅቱ የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክተር አቶ መለሰ በቀለ እንደገለፁት ይህ የአመራር ስነ-ምግባር የግናዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለመስጠት ቀደም ብሎ የታሰበ ቢሆንም ከኮሮና ወረርሽኝ ስጋቶች ጋር ተያይዞ እንዲራዘም ተደርጎ አሁን ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ለመስጠት እንደተወሰን ተናግረዋል፡፡

የድርጅት አመራር ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመታገል መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መለሰ ይህ ስልጠና ከፌዴራል ስነ- ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባር ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት የስነ ምግባር ስልጠና ባለሙያ በሆኑት ወ/ሮ ሜሮን ዳምጤ እንዲሰጥ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በየደረጃው ላሉ አመራርና ሰራተኞች ከፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሚመጡ ባለሙያዎች እና በድርጅቱ የስነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች በመስጠት ተመሳሳይ የግንዛቤ ደረጃ እንዲኖርና በተቀናጀ መልኩ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የመቅረፍ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በሥልጠናው የአመራር ስነ-ምግባር ምንነትን ጨምሮ የአመራር አይነቶች፣ሥነምግባር ለመሪዎች ለምን ጠቃሚ ሆነ? የሥነ ምግባራዊ አመራር ክህሎቶች (skills) እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው መሰረተ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን በባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በተያያዘም ከስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች እንደ ድርጅቱ ተጨባጭ ሁኔታ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ አግኝተዋል፡፡
በየግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው የተሳተፉትና በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ድርጅቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ለአመራሩ እንዲህ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸውና በተዋረድ ለሌሎች አመራርና ሰራተኞች ሊሰጥ እንደሚገባ ገልፀው አመራሩ ውጤታማ የአመራር ሥነ-ምግባርን ተግባራዊ በማድረግ የድርጅቱን ራዕይ እውን ሊያደርግ የሚያስችል የተሻለ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡