ድርጅቱ ኤጀንሲው ቀደም ሲል በስድስት ወራት አፈፃፀም ላይ ባደረገው የግምገማ ግብረ መልስ የተሰጡ ሀሳቦችን ተኩረት ሰጥቶ ለማስተካከል የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2013 የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም በቁልፍ የአፈፃፀም መለኪያዎች ተገምግሞ በጥንካሬ፣ በክፍተት የታዩ እንዲሁም በቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን የትኩረት ሥራዎች ባካተተ መልኩ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደደር ኤጀንሲ በማኑፋክቸሪንግ እና ኢነርጂ ሴክተር የተዘጋጀ ግብረ መልስ ሚያዚያ 29/2013 ዓ.ም በድርጅቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ቀርቧል፡፡
የኤጀንሲው ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ እና ሌሎች ከፍተኛ የአጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች እንድሁም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላትና የመሰረታዊ ሰራተኞች ማህበር ተወካዮች በተገኙበት በአፈፃፀም ግብረ መልስ ዙሪያ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የድርጅቱ የምርት፤የሽያጭ፤የትርፍ/ የኪሳራ ዕቅድ አፈፃፀም እና የደርጅቱ የፋይናንስ አፈፃፀም በግብረ መልሱ ከታዩ ዋና ዋና ጠንካራ ጎኖች ሲሆኑ የፕሮጀክት አፈፃፀም ፤ተሰብሳቢ ሒሳብ ፤የካፒታል በጀት ዕቅድ አፈፃፀም በአፈፃፀም ከታዩ ክፍተቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በተያያዘም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እና መለዋወጫ ችግሩን ለመፍታት ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር በመደራደር እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ እጥረት ከባንኮች ጋር በመነጋገር እና በመወያየት ችግሩን በመፍታት ምርታማነትና የሽያጭ ገቢን ማሳደግ፤የሪፎርም ሥራዎች ችግር ፈቺና ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ሆነው እንዲተገበሩ ማድረግ፤የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም በመገንባትና ተሞክሮ በመውሰድ የፕሮጀክት አፈፃፀምን ማሻሻል፤የውጪ ምንዛሪ ክትትል በማድረግ የካፒታል ግዢዎችን በዕቅዱ መሠረት እንዲከናወኑ ጥረት ማድረግ ፤የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የተጀመረውን ሥራ ማጠናከር ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሆኑ በግምገማው ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በቀረበው የኤጀንሲው የአፈፃፀም ግምገማ ግብረ መልስ ላይ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ብሎም አሁን ካለው የገበያ ውድድር ተመራጭ ለመሆን ክፍተቶቹን በማረም እንደሚሰራ ገልጸው የኤጀንሲውን እገዛ የሚፈልጉ ጉዳዮች በመኖራቸው ኤጀንሲው የራሱን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በግምገማ ግብረ መልሱ ማጠቃለያ የኤጀንሲው ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ እንደገለፁት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ያጋጠሙትን ችግሮች ተቋቁሞ አትራፊ ሆኖ መቀጠሉ የአጠቃላይ ሰራተኛው፣የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ፣የሥራ አመራር ቦርዱና ማኔጅመንቱ የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቁመው ኤጀንሲው ቀደም ሲል በስድስት ወራት አፈፃፀም ላይ ባደረገው የግምገማ ግብረ መልስ የተሰጡ ሀሳቦችን ተኩረት ሰጥቶ ለማስተካከል የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑንና ለተሻለ ውጤት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡