የብርሃንና ሰላም ህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በህትመት ዘርፍ በሙያ ብቃት ምዘና ጣቢያነት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ዋንጫና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበረከተለት

ሽልማቱ ኮሌጁ በህትመትና ተዛማጅ ሙያ ዘርፍ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ከማፍራት አንፃር የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅም እንደሚሆነው ተገልጿል፡፡

በአገራችን የሚስተዋለውን በትምህርትና ሥልጠና የታገዙ ብቁ የህትመት ባለሙያዎች እጥረት በመቅረፍ ዘርፉን በማዘመን ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ብርሃንና ሰላም ህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በዋናነት ከሚሰጣቸው የህትመት ቴክኖሎጂ፣ ግራፊክ አርት እና የህትመት ዋጋ ትመና ሥልጠናዎች ባሻገር በዘርፉ የሙያ ብቃት ምዘና ጣቢያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡

ኮሌጁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የስልጠና ፍላጎት ለማርካት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ከማከናወንና በትምህርትና ስልጠና የታገዘ ብቁ ባለሙያ ከማፍራት በተጓዳኝ የሙያ ብቃት ምዘና ጣቢያነት መስፈርት አሟልቶ በዘርፉ ብቸኛው የምዘና ጣቢያ መሆኑን የኮሌጁ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ካሳ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ባለስልጣን የኮሌጁን ብቃት በመረዳት ኮሌጁን የሙያ ብቃት ምዘና ጣቢያ አድርጎ ከመጠቀሙም በላይ ተመዛኞችን ሲልክ የምዘና ሂደቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን አስፈላጊ የመመዘኛ ግብአቶችን በማሟላትና አስተባባሪዎችን በመመደብ ብሎም የመመዘኛ ወርክሾፖችን ዝግጁ በማድረግ ለነበረው አስተዋፅኦ ሽልማቱ እንደተበረከተለት የገለፁት የኮሌጁ ዳይሬክተር የተሰጠው እውቅና ለተሻለ ኃላፊነት እንዲሰራ ያተጋዋል ብልዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ለኮሌጁ ለተበረከተው እውቀናና ሽልማት አመስግነው በሽልማቱ መላው የኮሌጁ ባልደረቦች መደሰታቸውን የገለፁ ሲሆን ሽልማቱ ኮሌጁ በህትመትና ተዛማጅ ሙያ ዘርፍ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ከማፍራት አንፃር የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅም እንደሚሆነው ገልፀዋል፡፡