የድርጅቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር እና14001:2015 የአካባቢ ደህንነትን ከሌሎች የአሰራር ስርዓቶች በጥምረት እንዲተገበሩ የተጀመረውን ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ተገለፀ፡፡
ከ2009 እ.ኤ.አ ጀምሮ የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ሰርቲፊኬቱ ባለቤት መሆን የቻለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ስርዓቱን መተግበርና ማስቀጠል በመቻሉ አሁንም ተሸላሚ መሆኑን የጥራት ስራ አመራርና ማረጋገጫ ቡድን መሪ አቶ ኪዳኑ ነጋሽ ገልፀዋል፡፡
ጀርመን ሀገር የሚገኘው እና እ.ኤ.አ 1985 የተመሰረተው ዲ.ኪው.ኤስ የተሰኘ ተቋም ሰርቲፊኬቱን እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ኪዳኑ አንድ ጊዜ የተሰጠ ሰርቲፊኬት ለሦስት ዓመት የሚያገለግል ሆኖ በየዓመቱ የክትትል ሥራና ግምገማ ይደረግበታል ብለዋል፡፡ በተያያዘም ሰርቲፊኬቱን ለማግኘት የተቀመጡ መስፈርቶች ደንበኛ ተኮር መሆን፣ አመራር ተኮር፣ ሰራተኞችን ማሳተፍ የተካተቱባቸው 7 መርሆች እና የድርጅት ነባራዊ ሁኔታ ፣ አመራር ፣ዕቅድ ፣ድጋፍ እና አፈጻጸም የተካተቱበት 10 መስፈርቶች እንደተቀመጡና ድርጅቱ ይህን ሰርቲፊኬት ያገኘው በተቀመጡት መርሆችና መስፈርቶች መሰረት ሥራዎችን በመስራቱና በውጪ ኦዲተሮች ተገምግሞ በመረጋገጡ ነው ብለዋል ፡፡
እንደ አቶ ኪዳኑ ገለፃ የሰርቲፊኬት ባለቤት ለመሆን በተቋሙ የታለመ ዓላማ ወይም ዕቅድ 80% እና ከዚያ በላይ መፈጸምና ይህንኑም በቀጣይነት ማሳካት እንደሚኖርበትና ድርጅቱ የሰርተፍኬት ባለቤት መሆኑ የደንበኛ ርካታን ለማሳደግና ደንበኞች በድርጅቱ ላይ ያላቸውን እምነት ለማሳደግ፣ ትርፍን፣ የገበያ ድርሻን ለማሳደግና ለሚፈጠሩ መልካም ዕድሎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፤ የሥራ ሂደቶችን እርስበርስ ለማስተሳሰርና ምርታማነትን ለማሳደግ፤አጠቃላይ አፈጻጸምን ለማሻሻል እና ወጭን ለመቀነስ ፤ባለድርሻ አካላት በድርጅቱ ላይ ያላቸውን እምነት ለማሳደግ ድርጅቱ በገበያ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ለማሳደግ ፤ግባአቶችን በአግባቡ በመጠቀም የማምረቻ ወጭን ለመቀነስ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይ መስፈርቱን በማሟላት ሰረተፊክቱን እንዲታደስ ለማድረግ በISO በውስጥና በውጭ ኦዲት የሚሰጡትን የማሻሽያ ሃሳቦችን በወቅቱ ማከናወን፤ስርዓቶችን በሁሉም ሠራኞች ግንዛቤ እንዲፈጠር ጠንክሮ መስራት፤ሁሉም ስራዎች በተዘጋጁ መመሪያዎች፣ፕሮሲጀሮች፣ቅጾች እና ቼክ ሊስቶች መሰረት መሰራታቸው ክትትል ማድረግ እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ ማሻሽያ የሚያስፈልጋቸው ሰነዶች እንዲሻሻሉ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የህዝብ ግንኙነትና ማህበራዊ ጉዳዮች ፅ/ቤት ድርጅቱ የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ሰርቲፊኬት ባለቤት በመሆኑ ለመላው የድርጅቱ አመራና ሰራተኞች እንኳን ደስ ያላችሁ እያለ ለበለጠ ሥራና ስኬት በተሻለ መነቃቃት እንድንሰራ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡