ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት በዕቅድ አፈፃፀም አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ

ድርጅቱ የተለያዩ ወቅታዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለዚህ ውጤት መብቃቱ የአመራሩን ቁርጠኝነት ብሎም የሚሰጠውን አቅጣጫን ተግባር ላይ የሚያውል ታታሪ ሰራተኛ መኖሩ ማሳያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ሐምሌ 23/2014 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል በተዘጋጀው የግምገማና የውይይት መድረክ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉልን ጨምሮ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እና የማኔጅመንት አባላት፤ቡድን መሪዎችና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች የተገኙ ሲሆን የድርጅቱን የ2014 በጀት ዓመት ሥራ አፈፃፀም ሪፖርትንና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ተገምግሟል፡፡

የድርጅቱ የዕቅድ ዝግጅትና ፕሮጀክት ክትትል አገልግሎት ኃላፊ አቶ መኮንን አበራ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በ2014 በጀት ዓመት ከዕቅድ አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት ተገልፀዋል፡፡

እንደ ሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ በገንዘብ ብር 270,604,463 የሚገመት ምርት ለማምረት ታቅዶ ብር 325,374,110 የሚያወጣ ምርት ለማምረት መቻሉንና አፈፃፀሙም በመቶኛ 120.24% መሆኑ ተገልጿል፡፡ የምርት አፈፃፀሙ ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር በብር 54,769,647 ወይም በ20.24%  ከፍ ብሎ መከናወኑን በዕለቱ የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ በ2014 በጀት ዓመት በሽያጭ ገቢ ብር 540,559,000 ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ብር 690,206,107 በማግኘት  በመቶኛ 127.68% ውጤት ሊመዘገብ ችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ክንውኑ ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር በብር 149,647,107 ወይም በ27.68% ከዕቅድ በልጦ መከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ድርጀቱ በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበውን ትርፍ ሲታይ ከታክስ በፊት ብር 183,316,914 ለማግኘት ታቅዶ ብር 220,325,724 በመሆኑ በመቶኛ 120.19% ያስመዘገበ ሲሆን ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር በብር 37,008,810 ወይም በ20.19% ከፍ ብሎ መከናወኑን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከዋናው ኦፕሬሽናል ሥራዎቹ ጎን ለጎን ከሚያከናውናቸው የአመራርና ሰራተኞች አቅም ግንባታ ሥራዎች መካከል ሥልጠና ይጠቀሳል፡፡ በበጀት ዓመቱ 407 ሰራተኞችን ለማሰልጠን ታቅዶ 948 ሰራተኞች ስልጠና እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን ለእነዚህም ስልጠናዎች በጠቅላላው ብር 237,560 ወጪ ሆኗል፡፡ በተያያዘም በድርጅቱ ደንብ መሰረት ትምህርት እንዲማሩ ፈቃድ ለተሰጣቸው ለ 53 ወንድና 34 ሴት በጠቅላላው 87 ሠራተኞች የትምህርት ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ለዚህም ብር 560,840.60 ወጪ ሆኗል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተኪ ሰራተኞችና ኃላፊዎችን በማብቃት ለ38 ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተኪነት በተመረጡበት የሥራ መደቦች ላይ በልዩ ልዩ ጊዜያት በውክልና ተመድበው እንዲሰሩ በማድረግ ከተመረጡበት ሥራ ጋር በተያያዘ በተግባር ልምምድ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ተደርጓል፡፡

የድርጅቱን የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ብር 1,063,500 ወጪ መደረጉን ተገልፆ በተያያዘም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ከሠራተኛውና ከማኔጅመንቱ በተደረገው የአንድ ወር የደመወዝ መዋጮ፣ ለ100ኛ ዓመት የድርጅቱ በዓል ለድግስ ዝግጅትና ለሌሎች ኘሮግራሞች ሊውል ከነበረው ገንዘብ፣ ከመሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር፣ ከሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር፣ ከሠራተኞች ክበብ አገልግሎት ኮንትራክተር በድምሩ ብር 10,240,000 እንዲሰበሰብ ተደርጎ 4.5 ሚልዮን ለመከላከያ ሰራዊታችን ቀሪው ደግሞ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በዓይነት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ድርጅቱ በ2014 በጀት ዓመት ያስመዘገበው ውጤት የሚያስደስት መሆኑን ተገልፆ በተጀመረው በጀት ዓመትም ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በተለዩ ችግሮች ላይ የመፍትሄ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በግምገማና ውይይት መድረኩ ከተሳተፉ አመራሮች ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች በሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በተመለከተ  ዋና ዋና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነና ድርጅቱን ዘመናዊና የዲጂታል ህትመት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ፤ በጥራትና በማስረከቢያ ጊዜ አጠባበቅ የሚታዩ ቅሬታዎችን በመቅረፍ ደንበኞች ፍላጎት ማሟላት፤በውጭ ሀገር የሚታተሙ ህትመቶችን በተወሰነ ደረጃ በድርጅታችን እንዲታተሙ ማድረግ፤ደንበኛው በፈለገው ወቅት ወዲያው አትሞ መስጠት /on demand print) የሚያስችል ቴክኖሎጂና የአሰራር ስርዓት መተግበር፤ ዲጂታል የግብይት ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ፤የሰው ሃብት ብቃትን ማሳደግ፤ ከህትመት ውጭ ሌሎች የገቢ ምንጭ አማራጮችን ማፈላለግ፤ ወጪዎችን በመቆጠብ ትርፋማነት ማሳደግ የሚሉ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡  በምርት ብር 295,455,000የሚገመት ለማምረት፣  በሽያጭ ብር 579,323,000 በማግኘት ትርፍ ከታክስ በፊት ብር 187,779,000 ለማግኘት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በ2014 በጀት ዓመት ላይ የተመዘገበው ውጤት ከሥራ አመራር ቦርዱ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ሠራተኞች ጥረት ውጤት መሆኑን ገልፀው ባጠቃላይ ለመጣው ውጤት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አክለውም በውይይቱ መድረኩ የተነሱ ገንቢ ሀሳቦች ድርጅቱ በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ብሎም ለድርጅቱ ቀጣይነት ግብዓት በሚሆኑበት አግባብ ተግባር ላይ ሊውሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል የዕለቱን የግምገማና የውይይት መድረክ ባጠቃለሉበት ወቅት ድርጅቱ ካሉበት በርካታ ጫናዎች አንፃር አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀው ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በመናበብ እና በኃላፊነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡