ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አመራርና ሠራተኞች በገቢ ግብር አዋጅ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

ስልጠናው በግብር አዋጅ አፈፃፀም ላይ የሚመለከታቸው ሠራተኞች የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና አዋጁን በተቀመጠው አግባብ ተፈፃሚ ማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡

የአንድ ድርጅት ውጤታማነት ከሚለካባቸው ጉዳዮች መካከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የአሰራር ሂደትን የሚቃኙ አዋጆች፣ ደንብና መመሪያዎች በሚገባ መተግበሩ አንዱ ነው፡፡ በድርጅቶች የሚገኙ የፋይናንስ ሥራዎች የሚመሩበት በአገር አቀፍ ደረጃ በተዋረድ የተለያዩ መመሪያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡

ብርሃንና ሰለም ማተሚያ ድርጅት የሀገርን ኢኮኖሚ እንደሚደግፉ ከታመነባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች አንዱ ሲሆን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ሚና ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ በህግና ስርዓቱ መሰረት ግብር መክፈሉ ነው፡፡

ስልጠናው በፋይናንስ አሰራር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ከመጫወቱም በላይ አዋጁን በተቀመጠው አግባብ እንዲተገበር በማድረግ ረገድ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖር እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

በሶስት ዙር በገቢዎች ሚኒስቴር ባለሙያዎች በተሰጠው ስልጠና የድርጅቱ ፋይናንስ፣ ሰው ሀብት ሥራ አመራርና ልማት፣ ማርኬቲንግ ዳይሬክቶሬት፤የውስጥ ኦዲት እና የህግ አገልግሎት ባልደረቦች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ስልጠናው በ2009 ዓ.ም የተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በስልጠናው የተሳተፉ የድርጅቱ ሠራተኞች እንደገለፁት ስልጠናው ቀደም ሲል በተልምዶ የሚሰሩ አሰራሮችን በማስቀረት ወጥና ዘመናዊ፤ አዋጁን መሰረት ያደረገ አሰራር ለመከተል ያስችላል ብለዋል፡፡

ወሪ/ት ስመኝ ማሞ የፋይናንስ ከፍተኛ አካውንታንት ባለሙያ ሲሆኑ ስልጠናውን ከተሳተፉ የፋይናንስ ባልደረቦች አንዷ ናቸው፡፡ በስልጠናው ዙሪያ በሰጡት አስተያየት የሚመለከታቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ይህን መሰል ስልጠናዎች መሰጠቱ ሊኖሩ የሚችሉ ብዥታዎችን ለማጥራትና ህጉን የተከተለ ውጤታማ ስራን ለመስራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

ወ/ሪት ስመኝ አያይዘውም በስልጠናው ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በቂ ግንዛቤ ማግኘት እንደቻሉ ገልፀው በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ ለማድረግም መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

የድርጅቱ የገንዘብ አሰባሰብና ክፍያ አፈፃፀም ቡድን መሪ አቶ ደበበ ወ/ሰንበት እንዳሉት ስልጠናው በገቢዎች ባለሙያዎች እንደተሰጠና ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ አመራርና ሰራተኞች በሶስት ዙር እንደተሳተፉበት ገልጸው በየዙሩ ማጠናቀቂያ ላይ ምዘና እንደነበረው ጠቁመዋል፡፡ አቶ ደበበ አክለውም ስልጠናው በልምድ የሚሰሩ ነገሮችን ወቅታዊ ከሆነው መመሪያና ህግ አንጻር በመፈተሽ ለማስተካከል አንደሚረዳና ሠራተኞች ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡

ቡድን መሪው ስልጠናው በፋይናንስ አሰራር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ከመጫወቱም በላይ አዋጁን በተቀመጠው አግባብ እንዲተገበር በማድረግ ረገድ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ የሰው ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ታመነ ዘውዱ በበኩላቸው አስራ አምስት ቀናት በዘለቀው ስልጠና ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ሠራተኞች እንዲሳተፉ መደረጉንና በቂ ግንናዛቤ መጨበጣቸው በምዘና እየተረጋገጠ ማጠቃለያው ላይ መደረሱን ገልፀው፤ በቀጣይም እድሉን ያላገኙ የሚመለከታቸው ሠራተኞች ይህንን ጠቃሚ ስልጠና እንዲወስዱ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ብዙ ግዜ ከግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ ለሚመጡ ችግሮች ምኝጭ የግንዛቤ ክፍተት እንደሆነ ጠቅሰው አዋጁን በተቀመጠው አግባብ ተፈፃሚ ማድረግ ስለሚገባ የግናዛቤ ማስጨበጥ ስልጠናው እንደተሰጠ ተናግረዋል፡፡ በተገኘው ግንዛቤ መሰረት እስካሁን በድርጅቱ ሲሰራባቸው የቆዩ አሰራሮች አሁን ካለው በስልጠናው ከተጨበጠው ሀሳብ ጋር በንፅፅር በማቅረብ ክፍተቶች ካሉ የማስተካከያ ሥራ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ አክለውም ስልጠናውን ለሰጡት የገቢዎች ሚኒስቴር ባለሙያዎች በድርጅቱ ስም ምስጋና አቅርበው በቀጣይ ከገቢ ግብር ጋር ተያያዥነት ያለው ሥራ የሚሰሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ውይይት በማድረግ አዋጁን ተፈፃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡