የአደጋ ጊዜ አወጣጥ ልምምዱ በቀጣይም በተወሰነ ጊዜ ርቀት እንደሚደረግና ማንኛውም ሠራተኛ አደጋ መድረሱን የሚጠቁም ድምፅ (አላርም) በሰማ ጊዜ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባው ተገልጿል፡፡
መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ልምምድ ላይ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላትና አጠቃላይ ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን ሰራተኞች ከየስራ ገበታቸው የአደጋ ጊዜ መውጫዎችን በመጠቀም ወደ አደጋ ጊዜ መሰብሰቢያ ቦታ እንዲሰባሰቡ ተደርጓል፡፡
አደጋ መቼ እና በምን ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ስለማይታወቅ አደጋን እንዲከሰት ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን በማጥናት የቅድመ መከላከል ሥራዎች መሥራት እንዳለ ሆኖ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ደግሞ አደጋው በሰራተኞችና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መቆጣጠርን ዓላማው ያደረገ ልምምድ እንደ ነበር የድርጅቱ ከፍተኛ የሰራተኞች ደህንነት ባለሙያ አቶ ጌታው ይርጋ ገልፀዋል፡፡
አቶ ጌታው አያይዘውም ልምምዱ አደጋ እንደተፈጠረ ታሳቢ ተደርጎ በተቋቋመው የአደጋ ጊዜ አወጣጥ ልምምድ አስተግባሪ ኮሚቴ አማካኝነት የተካሄደ እንዲሁም ቀደም ሲል በተሰሩ በአደጋ ጊዜ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች የተደራጀ ሲሆን አጠቃላይ ሠራተኛው ለአደጋ ጊዜ የሚሰጡትን ምላሽ ለመረዳት የሚያስችል መረጃ ተገኝቶበታል ብለዋል፡፡ አክለውም በአደጋ ጊዜ አወጣጥ ልምምድ መርሃ ግብሩን ያስተባበሩ ሰራተኞችን እንዲሁም አስተባባሪዎች ለሰጡት አቅጣጫ በጎ ምላሽ የሰጡትን አጠቃላይ ሠራተኞች አመስግነው በልምምድ ወቅት የተስተዋሉ አጠቃላይ ጉዳዮችን የሚገልፅ ሪፖርት ለድርጅቱ እንደሚቀርብና ከተለያዩ አደጋዎች ጋር የተያያዙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በልምምዱ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንደገለጹት ልምምዱ የተካሄደው አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ አጠቃላይ ሠራተኞች ባጠረ ጊዜ በአደጋ ጊዜ መሰብሰቢያ ቦታ ላይ ተሰባስበው አስተባባሪዎች ማለትም የድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ስልጠና የወሰዱ ሠራተኞች በሚሰጡት መመሪያ መሰረት በአፋጣኝ ችግሩን ለመፍታት ልምምድ ለማድረግ እንዲቻል መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
ይህ አይነቱ ልምምድ በተለያዩ ተቋማት እንደሚተገበር የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በድርጅቱም በየበጀት ዓመቱ በተወሰነ ጊዜ ርቀት እንደሚደረግና ማንኛውም ሠራተኛ አደጋ መድረሱን የሚጠቁም ድምፅ (አላርም) በሰማ ጊዜ ፈጣንና ራስን፣ የሥራ ባልደረቦቹንና ድርጅቱን ከአደጋው ለመታደግ በሚያስችል መልኩ ምላሽ መስጠት እንደሚገባው አሳሳበው በልምምዱ የተሳተፉ የድርጅቱን ሠራተኞች አመስግናዋል፡፡