የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች ያሉትን የትምህርት ዕድል አማራጮች በመጠቀም ራሳቸውን ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

መጋቢት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስርያ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በጀመረው የበዓል አከባበር ስነ-ስርዓት የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ (ድጋፍ ዘርፍ) አቶ በላይ ኪዳኑን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት እና ከየሥራ ክፍሉ የተውጣጡ ሴት ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በበዓል አከባበሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በላይ ኪዳኑ ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጫና ለማስቀረት ዋጋ የተከፈለ በመሆኑንና አሁን ላይ ያለውን አንፃራዊ መሻሻል ለማስቀጠል ሴቶች ራሳቸውን በማንቃት (በመማር) በመደራጀት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ወንዶችም ሴቶች ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርጉትን የስኬት ጉዞ በማገዝ ረገድ ከጎን በመቆም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የድርጅቱ የስርዓተ ፆታ ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተ/ሃይማኖት በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ47ኛ ጊዜ እንዲሁም በድርጅቱ ለ17ኛ ጊዜ “ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለፆታ እኩልነት እንቀበል” በሚል መሪ ቃል በተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መብትና እኩልነትን በማስከበር ረገድ የሴቶችን ትግልና እንቅስቃሴ የሚዘከርበት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ ሄለን ለበዓሉ የተዘጋጀውን “ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለፆታ አኩልነት” የሚል ርዕስ የያዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለበዓሉ ታዳሚዎች ያቀረቡ ሲሆን በስልጠናው ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ ዓለም ዓቀፍ እና ሀገር አገፍ እውነታዎች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
ከስልጠናው በኋላ ተሳታፊዎች በተለያዩ ጉዳዮች ውይይት ያደረጉ ሲሆን ሴቶች ራሳቸውን እንዲለውጡና ስኬታማ እዲሆኑ የሚያስችል ቃል የመግባት መርሃ ግብር ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች ያሉትን የትምህርት ዕድል አማራጮች በመጠቀም ራሳቸውን ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የበዓል አከባበሩን መደምደሚያ የነበረው በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም የተደረገው ጉብኝት ሲሆን ተሳታፊዎች በስልጠናው ከተነሱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች አንፃር ሀገራችን ያለችበትን ደረጃን በዘርፉ እየተሰራ ያለውን ሥራ ያስቃኘ እንደነበር መረዳት ተችሏል፡፡