የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት ያስሚን የሀብረዲ የተመራ  የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሥራ ጉብኝት አደረገ

ጉብኝቱ በድርጅቱ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ግንዛቤ ያስጨበጠ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በሥራ ጉብኝቱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት ያስሚን የሀብረዲን ጨምሮ ማኑፋክቸሪንግ ሴክተር የፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር ወ/ሮ አስማ ረዲ እና የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ፣ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችና የማኔጅመንት አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ለመጡት የሥራ ኃላፊች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትን የተመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዮች የተካተቱበት ገለፃና በስራ ክፍሎች የሚደረግ ጉብኝት የዕለቱ መርሃ ግብር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገው የሥራ ጉብኝት ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ ያለፈባቸውን አበይት የታሪክ ሂደቶች እንዲሁም አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴውን የሚያሳይ ገለፃ በድርጅቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ታደሰ የቀረበ ሲሆን  በዋናው መስሪያ ቤት የሚገኘውን የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የንድፈ-ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና መስጫ ቦታዎች፤ በመደበኛና በሚስጥራዊ ህትመት ክፍሎች የቅድመ ህትመት የህትመትና የድህረ ህትመት ሥራ ክፍሎች እንዲሁም አቧሬ ቅርንጫፍ የህትመት ግብዓቶች ማከማቻ መጋዘን ጉብኝት ተደርጎባቸዋል፡፡

የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የጎበኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት ያስሚን የሀብረዲ ድርጅቱ ያለው የሥራ አፈፃፀም የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው በህትመት ዘርፉ ያሉትን ተጨማሪ ሥራዎች በመስራት የሀገሪቱን ብሎም የጎረቤት ሃገራትን   የህትመት ፍላጉት ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችል አቅም መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበው  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግም የድርጅቱ ራዕይ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

በጉብኝቱ ማጠቃለያ የተመለከቱትን መልካም አፈፃፀምና ለዚህም የተሻለ አፈፃፀም የድርጅቱ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ጥረትና የሥራ ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን በመግለፅ ይህው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ለድርጅቱ  ውጤታማነት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ቃል በመግባት የዕለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡