የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተሳትፎ አደረጉ

ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ500 በላይ የሚሆኑ የድርጅቱ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከተሰማራበት የህትመትና ተዛማጅ ሥራዎች ጎን ለጎን ማህበረሰቡን በተለያዩ አግባቦች ለመደገፍ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራን በዕቅድ አካቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዘርፉ ከሚሰራቸው በርካታ ሥራዎች መካከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ይገኝበታል፡፡

ድርጅቱ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሸገር ከተማ አስተዳደር በኮራ ጅዳ ክፍለ ከተማ ድሬ ሰኮሩ ወረዳ ልዩ ስሙ ድሬ ግድብ እየተባለ በሚጠራ ስፍራ ለ20 ተከታታይ ዓመታት ባከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ መርሃ ግብር የላቀ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በሀገር በአቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ሥራ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርገው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለበርካታ ዓመታት በሰራው ሥራ አካባቢው ቀደም ሲል ከነበረው የአፈር መሸርሸር ከመግታት ብሎም የተሻለና ያማረ ገፅታ እንዲኖረው ከማድረግ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን የአየር ንብረት ከማስተካከል አንፃር የድርሻውን አበርክቷል፡፡

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል በተደረገው ንቅናቄ ድርጅቱ ከበርካታ ዓመታት በፊት የጀመረውን የችግኝ ተከላና እንክብካቤ አጠናክሮ ለማስቀጠል ችሏል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ድርጅቱ ከሚያከናውናቸው የተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች አንዱ በሆነው የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ተግባር ላይ ለ20 ተከታታይ ዓመታት በትኩረት እየሰራ እንደሆነና በመንግስት የተቀመጠውን ሀገራዊ ፋይዳ ያለው የችግኝ ተከላ እቅድ እውን እንዲሆን እንደ አንድ ኃላፊነት እንዳለበት መንግስታዊ ድርጅት አመራሩንና ሰራተኛውን በማስተባበር ተከላው እንደተከናወነ ገልፀዋል፡፡

የችግኝ ተከላው በየዓመቱ በሚካሄድ አንድ ቀን በሚከናወን መርሃ ግብር የሚገታ እንዳልሆነ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከአካባቢው ማህበረሰብ የጥበቃና እንክብካቤ ሥራን ሊሰሩ የሚችሉ ሠራተኞችን በመቅጠር እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገለት እንደሆነና በተወሰነ የጊዜ ልዩነትም የችግኞቹን ሁኔታ አካላዊ ምልከታ እየተደረገ ሪፖርት እንደሚቀርብ ተናግረው ቀደም ባሉ ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢውን ገፅታ ውብ ከማድረግ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ውጤት የተገኘበት እንደሆነና ሌሎች ተቋማት ተሞክሮ ሊወስዱበት በሚያስችል ደረጃ ስኬታማ ሥራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉ የድርጅቱ አመራሮች መካከል አቶ ዳኛቸው ገ/ወልድ የመደበኛ ህትመት ዳይሬክተር አንዱ ሲሆኑ በህትመት ላይ ለተሰማራ ድርጅት ወረቀት ዋነኛ ግብዓቱ መሆኑንና ለወረቀት ስራ ግብዓት የሚውለው ደግሞ ከደን ስለሚገኝ ድርጅቱ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ ላይ መሳተፉ በተዘዋዋሪ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የድርጅቱ ስርዓተ ፃታ ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሃማኖት ድርጅቱ ለተከታታይ ሃያ ዓመታት ባካሄደው የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሴት ሰራተኞች ተሳትፎ አመርቂ እንደሆነ ገልጸው በሀገራችን ለሚካሄዱት ማናቸውም የልማት ስራዎች ሴቶች እኩል ተሳትፎ እንዳላቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የድርጅቱ የመሰረታዊ ሰራተኞች ማህበር ስራ አስፃሚ አባል አቶ ሲሳይ ቤጊ በበኩላቸው ድርጅቱ በመንግስት መመሪያ መሰረት በእንዲህ መሰል የልማት እንቅስቃሴ ሰራተኞችን እንዲሳተፉ ማድረጉ የተሻለ መነቃቃትን መፍጠር እንደሚያስችል ጠቅሰው ለ20ኛ ግዜ በተካሄደው የችግኝ ተከላ የድርጅቱ አመራር፣የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር እና ሰራተኞች ለአንድ ሀገርን ብሎም ዜጎችን በሚጠቅም ዓላማ በጋራ መስራታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ በስፍራው ካካሄዳቸው 20 ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ውስጥ በ18ቱ ላይ ተገኝተው አሻራቸውን ማሳረፍ የቻሉት አንጋፋዋ የድርጅቱ ሰራተኛ ወ/ሮ ፋናዬ የችግኝ ተካለው ላይ መሳተፍ እንዳስደሰታቸውና ቦታው ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አንፃር በደን እየተሸፈነ መምጣቱን ማስተዋል መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡አያይዘውም ድርጅታቸው እንዲህ ባለው ሀገራዊ መልካም ተግባር ላይ መሳተፉ ደስ ያሰኛል ብለዋል፡፡

በእለቱ ከ1200 በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን እንደ ሀገር ለታቀደው 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር የመትከል እቅድ እንዲሳካ ድርጅቱ የበኩሉን መወጣቱን መረዳት ተችሏል፡፡