የድርጅቱ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች መካከል አንዱ በሆነው አገልግሎት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 የሚገኙ ሁለት አረጋውያን የቤት እድሳት የምረቃና የቁልፍ ማስረከብ ሥነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡
ታህሳስ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በተከናወነው የምረቃና ቁልፍ ርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፤ የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተቀባ፣ የክ/ከተማው ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፈቱራህማን ኸይረዲንን፣ የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች ፤ የወረዳ ዘጠኝ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መለስ ኑረዲን፤በየደረጃው የሚገኙ የክ/ከተማና የወረዳ አመራሮች፣ እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት፣የቤት ርክክብ የተረገላቸው ተጠቃሚዎችና የወረዳ ዘጠኝ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በኢትዮጵያ የህትመት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈር ቀዳጅና አንጋፋ መሆኑ ይታወቃል። ድርጅቱ በዘርፉ በላቀ ሁኔታ ከ100 ዓመታት በላይ በዘለቀው አገልግሎቱ በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን አሻራ ያሳረፉ የሀገር ባለውለታ መሆኑ በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን በህትመትና ተዛማጅ ሥራዎቹ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎቹ የህዝብ አለኝታነቱን ያስመሰከረ ታላቅ የህዝብ ሀብት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የወረዳ ዘጠኝ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መለስ ኑረዲን በበኩላቸው የአረጋውያንን ቤቶች በማደስና የተለያዩ በጎ ተግባራትን በማድረግ ከጎናቸው ለቆመውና 102 ዓመታትን ላስቆጠረው አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የአንበሳውን ድርሻ በመወጣቱ የምስጋና መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ በየበጀት ዓመቱ በእቅድ አካቶ ከሚያከናውናቸው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በመንግስት ለሚቀርቡ የድጋፍ ጥሪዎች ፈጣንና አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ ድርጅቱ በሚገኝበት አካባቢ ለሚኖሩና ድጋፍ ለሚሹ አረጋዊያን እና ወላጆቻቸውን በኤች አይቪ ኤድስ ላጡ ህፃናት ቋሚ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ገልፀው የድርጅቱን አቅም በፈቀደ ይህ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም በ2016 በጀት ዓመት ከመንግስት በወረደው አቅጣጫ መሰረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ከሚገኙ አቅመ ደካማ የሀገር ባለውለታ አረጋዊያን መካከል የሁለቱን ቤት 2.8 ሚሊዮን ብር ወጪ በመሸፈን የእድሳት ሥራም ያከናወነና ዋና ዋና የፈርኒቸር ቁሳቁሶችን በሟሟላት ማስረከቡን ገልፀው በስራው ሂደት ላይ የተሰተፉ አካላትን አመስግነው ቤት ለታደሰላቸው አረጋውያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸውን የጀመሩት የአራዳ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተቀባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችን ይህን የተቀደሰ ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ የቤቶቹን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ለባለእድለኞች ላስተላለፈልን አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በአስተዳደሩ ስም አመስግነዋል፡፡
በተያያዘም ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር፣ ከወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር፣የኢትዮጵያ መከላከያና ፖሊስ ጀግኖች ቬትራንስ አሶሴሽን ማህበር የእወቅና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ቤት ከታደሰላቸው አረጋውያን ሻለቃ ጀምበሬ ተሰማ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦች ለድርጅቱና ለዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ሽታሁን ዋለ የምስጋና የመፅሐፍ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡