ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር የሥራ ስምምነት ውል ተፈራረመ

ስምምነቱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች በመፃሕፍ አትሞ ለማሰራጨት እንደሆነ ተገልጿል።

ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ፅ/ቤት በተካሄደው የስምምነት  ፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ፤ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎች እና የሁለቱም ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በውል ፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተገለፁት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ውሳኔዎችን አሳትሞ ለማህበረሰቡ ለማድረስ እንዲችል ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይሁንና የህትመት ስራውን  ጨረታ ከማውጣት ሂደቱ ጀምሮ እስከ ስርጭት ድረስ የራሱ የሆነ ውጣ ውረድ እንደነበረው ገልፀው በህትመት ሥራ ያካበተ ልምድ ያለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አትሞ የማሰራጨትቱን ጉዳይ  በተሻለ ያከናውነዋል በሚል እምነት በተደረጉ ውይይቶች ስምምነት ላይ በመድረስ ወደ ተግባር ለመግባት እንዲቻል ውሉ እንዳስፈለገ ተጠቁሟል። 

በውሉም መሰረት ቀደም ሲል የታተሙትን እንደስፈላጊነቱ ደግሞ ለማተም እንዲሁም በቀጣይ የሚዘጋጁትን በማተም ለማህበረሰቡ በሽያጭ ተደራሽ ማድረጉ የድርጅቱ ኃላፊነት ይሆናል ተብሏል።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከድርጀቱ ጋር በጋራ ለመስራት እድሉን በመስጠቱ አመስግነው ድርጅቱ ከ102 ዓመታት በላይ በመደበኛና ምስጢራዊ ህትመት ሥራዎቹ ለበርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት በመንግስት በተወካዮች ምክር ቤት እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቀው የሚወጡትን አዋጆችና ደንቦችን አትሞ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡  

ዋና ሥራ አስፈፃሚውም አክለውም ቀደም ሲል ድርጅቱ ሲያከውናቸው እንደነበሩት የአዋጆችና ደንቦች ህትመትና ስራጭት ሥራ በተመሳሳይ የሰበር ሰሚ ውሳኔዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል በሚል እምነት የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።