ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2017 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር የበዓል መዋያ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 እና 09 የሚገኙ 200 አቅመ ደካማ አረጋውያንና ደጋፊ የሌላቸው ወገኖች በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡  

ጳጉሜን 4 እና 5 ቀን 2016 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እና በወረዳ 05 ወጣቶች ማዕከል አዳራሽ እንዲሁም ድጋፍ በሚደረግላቸው አረጋውያን ቤት ለቤት በተደረገ የድጋፍ መርሃ-ግብር የበዓል መዋያ  ለእያንዳንዳቸው ብር 2000 ድጋፍ ተደርጓል፡፡  በማህበራዊ ኃላፊነት ተግባሩ ለበርካታ ወገኖች አለኝታ የሆነው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑና ረዳትና ደጋፊ የሌላቸው ወገኖች በዓሉን በጥሩ ሁኔታ ያከብሩ ዘንድ ቀደም ሲል ያደርግ የነበውን የምግብ ግብዓት ድጋፍ እንደየ ፍላጎታቸው ያከብሩ ዘንድ ወደ ገንዘብ በመቀየር ድጋፍ  አድርጓል፡፡

 

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የመንግስትና የህዝብ እንደመሆኑ መጠን በሀገር ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር አቅም በፈቀደ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን በዕቅድ በማካተትና በጀት በመመደብ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተያያዘም  የተለያየ የጤና እክል ኖሮባቸው ከቤታቸው መውጣት ያልቻሉ አቅመ ደካማ አረጋውያንን ታሳቢ በማድረግ የድርጅቱ ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ አገልግሎት ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሐይማኖት ከድርጅቱ ከተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከወረዳው ባለሙያዎች ጋር በመሆን የበዓል መዋያ ድጋፉን ቤት ለቤት የማድረስና  አረጋውያኑን የመጎብኘት ሥራ ተከናውኗል፡፡