የተደረገው ድጋፍ ድርጅቱ በቋሚነት ለሚደግፋቸው አስራ ሁለት ተማሪዎች መሆኑ ታውቋል፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎቹ ለበርካቶች አርዓያ መሆን የቻለ መንግስታዊ የልማት ድርጅት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ከመንግስት ለሚቀርብለት የድጋፍ ጥሪ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ እና በቋሚነት ለአቅመ ዳካማ አረጋውያንና ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ታዳጊ ህፃናት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲሱን 2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ምክንያት በማድረግ ጳጉሜን 05 ቀን 2016 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መርሃ ግብር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፤የድርጅቱ የስርዓተ ፆታና ማህባራዊ አገልግለት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሃይማኖት፣የማኔጅመንት አባላት፣ የሰራተኞች ጤና አጠባበቅ ቡድን መሪ ሲ/ር አበባዩ መርዕድና ሰራተኞች እንዲሁም ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችና ወላጅ/አሳዳጊዎቻቸው ተገኝተዋል፡፡
በድርጅቱ ቋሚ የሆነና ትምህርታቸውን መሰረት ያደረገ ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች እንደየክፍል ደረጃቸው የትምህርት ዘመኑን በሙሉ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችና ወላጆች/አሳዳጊዎች በድርጅቱ ለተደረገላቸው ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሱን ያስረከቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ባስተላለፉት መልዕክት የህዝብ ሀብት የሆነው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከዋናው የህትመት ሥራና ተዛማጅ ሥራዎቹ ጎን ለጎን ማህበረሰቡን በመደገፍ ረገድ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነና በትምህርት ዙሪያ የሚደረግ ድጋፍ የነገ ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋን ከማፍራት አንፃር የተለየ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አክለውም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ በመከታተል ለውጤት እንዲበቁ ምክራቸውን ለግሰው ለዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡