የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የስራ ኃላፊዎች እና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የሪፎርም እና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፡፡ ውይይቱን የመሩት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ናቸው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ዓለም አቀፍ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አዝማሚያ እና ለኢትዮጵያ ያለው አንድምታ፣የኢኮኖሚ ሪፎርም አፈፃጸም ውጤቶች እና አዝማሚያዎች፣የሪፎርም ተጠባቂ ፋይዳዎች እና የዋና ዋና ፕሮጀክቶች አፈፃጸም በም/ዋና ስራ አስፈፃሚ ኦፕሬሽን ዘርፍ አቶ ጌታሁን ነጋሽ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተመሳሳይ የድርጅቱ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በስትራቴጂክ ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በኩል የቀረበ ሲሆን በምርት 97.43 በመቶ ፤በሽያጭ 92.88 እንዲሁም በትርፍ ከታክስ በፊት 103.10 በመቶ መፈፀሙ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት የተቻለና ድርጅቱ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አበረታች አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ላይም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በቀረበው ሰነድ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የሁሉም ተቋማት አፈፃፀም ድምር ውጤት በሃገር አቀፍ ደረጃ የታቀደው ለመፈፀም ግብዓት እንደሆነ ጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት በመንግስት የታቀደው የ100 ቀናት እቅድ የተሳካ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ ድርጅቱ በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ የተከናወኑ አበይት ጉዳዮችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡