የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ  የሠራተኞች  በዓል  በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

በበዓል አከባበሩ ለድርጅቱ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ቆይተው ከድርጅቱ በጡረታ ለሚለዩ አመራሮችና ሠራተኞች ስጦታና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 

104 ዓመታትን ያስቆጠረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ አልፎ ዘመናትን እንዲሻገር ካሰስቻሉት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ጠንካራ ሰራተኞች ስላሉት መሆኑ ይታመናል፡፡ ዛሬም የድርጅቱ ምርታማነት ያድግ ዘንድ የሰራተኞች ህብረት መጠናከር ተገቢ እንደሆነ በፅኑ ስለሚያምን በየጊዜው ከሚያደርጋቸው የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማዎች ባሻገር ዓመታዊ የሰራተኞች በዓል በሚል ስያሜ ሰራተኞች ስለድርጅታቸው እንዲመካከሩ፣ እንዲዝናኑ እንዲሁም በድርጅቱ በስራ ላይ ቆይተው ከድርጅቱ በጡረታ ለሚለዩ አመራሮችና ሠራተኞች እውቅና የሚሰጥበት መርሃ ግብር ያዘጋጃል፡፡

ህዳር 07 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የ2017 ዓመታዊ የሠራተኞች  በዓል ላይ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉልን ጨምሮ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ፤ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፤ የማኔጅመንት አባላት፤ የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮችና አጠቃላይ የድርጅቱ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

በበዓል አከባበሩ ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን  ያስተላለፉት   የድርጅቱ   ዋና   ሥራ   አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በምርት፣ በሽያጭ እና በትርፍ ጥሩ የሚባል አፈፃፀም መመዝገቡን ገልፀው በሁለተኛው ሩብ ዓመት በቂ  የሥራ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ፣ በመደበኛም ሆነ በምስጢራዊ ህትመት ድርጅቱ የተቀበላቸውን ሥራዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በግዜ አንዲወጡ በማድረግ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት በተሻለ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት ይቻል ዘንድ፣ በከፍተኛ መጠን በድርጅቱ ስቶር የተከማቹ ግብዓቶችን ወደ ምርት በመቀየር እንዲሁም የድርጅቱን የማምረቻ መሳሪያ አቅም በማሳደግ ረገድ እየተከናወኑ ያሉና የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የበጀት ዓመቱ እቅድ እንዲሳካ ሁሉም አመራሮችና  ሰራተኞች ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል በበኩላቸው የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም አመርቂ እንደነበረ አስታውሰው በ2017 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ አመትም ጥሩ የሚባል ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል በተመሳሳይ የድርጅቱ ሰረተኞች የ2017 በጀት ዓመት እቅድን እንደሚያሳኩ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ አክለውም መላው ሰራተኛ ለድርጅቱ እቅድ መሳካት ትልቅ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በበዓል አከባበሩ ለድርጅቱ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ቆይተው ከድርጅቱ በጡረታ ለሚለዩ አመራሮችና ሠራተኞች ስጦታና የእውቅና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን የድርጅቱ 104ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት የዳቦ ቆረሳ መርሃ ግብር ተከናውኗል፡፡