100ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዮ የምስረታ በዓል አከባበር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት 100ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዮ የምስረታ በዓል አከባበር አስመልክቶ ለተለያዩ ሚዲያዎች የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም በፅ/ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የድርጅቱ የ100 ዓመታት ጉዞና የምስረታ በዓል አከባበር ሂደቱንና ስለሚኖሩ መርሃ-ግብሮች እንዲሁም ጋዜጠኞች አጠቃላይ የድርጅቱን ሁኔታ አስመልከተው ላነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ዋና ስራ አስፈፃሚው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈፃሚው በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የዛሬ 100 ዓመት በ1914 ዓ.ም የተመሰረተ በመሆኑ በዚህ ወቅት በዓሉን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም በዓሉ የሚከበረው በዕለቱ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት አራት ወራት አስከ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወንና የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት እንደሆነ በመግለፅ በዛሬው ዕለት የበዓሉ አከባበር የመክፈቻ ስነ-ስርዓት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ላለፉት መቶ ዓመታት ድርጅቱ ለህብረተሰቡ የተለያዩ የህትመት አገልግሎቶችን በመስጠት ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያደርግ መቆየቱን የገለፁት አቶ ሽታሁን ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንፃር መጀመርያ ኋላቀር ከነበሩት ቴክኖሎጂዎች በየጊዜው የተሻሉና ወቅቱን የሚዋጁ የህትመት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎቱንና አሰራሩን በማዘመን ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ከዕድሜው አንፃር ያሉትን የህትመት ቴክኖሎጂዎች በዓለም ደረጃ የህትመት ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ አንፃር ሲታይ ብዙ የሚቀረው መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ስር ነቀል በሆነ መልኩ ቴክኖሎጂውን ለማዘመንና አሰራሩን ለማሻሻል በ2014 በጀት ዓመት ወደ 515 ሚልዮን ብር የካፒታል በጀት ተፈቅዶ 339 ሚልዮን ብር የሚፈጅ 14 ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎችን ለመግዛት የግዢ ሂደት በማጠናቀቅ የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ የተጠየቀባቸው የማምረቻ ማሽኖች መግዛት ከተቻለ የድርጅቱን ዓቅም አሁን ካለው በእጥፍ የሚጨምር በመሆኑ የምንሰጠው የህትመት አገልግሎት ጥራቱንና የማስረከቢያ ጊዜውን የጠበቀ ስለሚሆን የደንበኞችን ፍላጎት የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ያሉት አቶ ሽታሁን ከዚህ በተጨማሪም በውጭ አገር የሚታተሙ መደበኛና ሚስጢራዊ ህትመቶችን በማተም የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል ብለዋል፡፡

ዕድሜውን የሚመጥን ዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሰራር በመጠቀም በመደበኛና ሚስጢራዊ ህትመት የምንሰጠውን አገልግሎት በማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት በሚያስችል መልኩ ስራዎች አየተሰሩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሽታሁን ይህ እንዲሳካ የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እና ማኔጅመንቱ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ ለትምህርት፣ለጤና፣ለፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች የመንግስትና የግል ድርጅቶች የህትመት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በየጊዜው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን በቅርቡም ለመከላከያ ሰራዊት በነበረው የድጋፍ ፕሮግራም ላይ ድርጅቱ 3.5 ሚልዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 161 ሚልዮን ብር ለማትረፍ ታቅዶ አፈፃፀሙ 167 ሚልዮን ብር ከታክስ በፊት ማትረፍ የተቻለ መሆኑን እና 132 ሚልዮን ካሬ ሜትር ማተም መቻሉን በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት 941 ቋሚ ሰራተኞች እና ከ230 እስከ 300 የሚሆኑ ጊዜያዊና ኮንትራት ሰራተኞች በስራ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ የሚጠቀምባቸው የማምረቻ መሳርያዎች፣መለዋወጫዎችና ግብዓቶች ከ90 ፐርሰንት በላይ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ናቸው ያሉት አቶ ሽታሁን የድርጅቱ ዋነኛ ተግዳሮት የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው መጠን አለማግኘት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ 100ኛ ዓመት የበዓል አከባባር ለሚቀጥሉት አራት ወራት የፓነል ውይይት በማካሄድ፣ደም በመለገስ፣የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ፣የድርጅቱን ታሪከዊ ጉዞ የሚያሳይ ኤግዚብሽን በማዘጋጀት፣ማህበራዊ ኃላፊነትን እና ሌሎች ተግባራቶችን በማከናወን የሚከበር ሲሆን የበዓሉ ማጠቃለያ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሆነ ከወጣው ፕሮግራም ለማወቅ ተችሏል፡፡