የህፃናት ማቆያ ማእከሉ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፤ የማናጅመንት አባላትና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራ
ሮች በተገኙበት ጥቅምት4/2012 ተመርቋል፡፡
የህፃናት ማቆያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በማቋቋም በተለይ በሴት ሰራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቀነስ፤ የሴቶችን ምርታማነት ለማሳደግና ህፃናት በቂ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያገኙ ማስቻልን ዓላማው አድርጎ እንደተቋቋመ የድርጅቱ ስርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄለን ተ/ሃይማኖት አስታውቀዋል፡፡
የድርጅቱ ስርዓተ ፆታ ዳይሬክተሯ እንደገለፁት በድርጅቱ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው በሚመለሱበት ወቅት በሚሰሩበት ተቋም ህፃናት ልጆቻቸውን በቅርበት እየተከታተሉና እየተንከባከቡ በተመደቡበት የሥራ ቦታ ያለምንም ሥጋት በሙሉ ትኩረት መስራት እንዲችሉ ህፃናት ልጆቻቸውን የሚውሉበት በህፃናት እንክብካቤ የሰለጠነ ባለሙያ የተካተተበት ማዕከል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ሄለን ገለጻ ማእከሉ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት እስከ አንድ አመት ከዘጠኝ ወራት እድሜ ያላቸው ሕፃናትን ተቀብሎ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የህ
ፃናት እንክብካቤ ባለሙያዋ ወ/ሮ አልማዝ መስፍን በበኩላቸው በማእከሉ ለሚገኙ ህፃናት ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልፀው ህፃናቱ ሊያርፉባቸው የሚችሉ የራሳቸው ፍራሾችና መጫወቻ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለሙያዋ አክለውም ለማዕከሉ የተዘጋጀው ክፍል ፀጥታው እና የክፍሉ ሁኔታ የህፃናቱን ምቾት ታሳቢ ተደርጎ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የበለጠ ምቹ ለማድረግ እንዲቻል ከወላጆችና ከባለሙያዎች አስተያየቶችን እና ጥቆማ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙ ልጆቻቸውን በማዕከሉ የሚያውሉ ሰራተኞች በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ መከፈቱ እንዳስደሰታቸው እና የልጆቻቸው በእንክብካቤ መቆየት በተረጋጋ መንፈስ ስራቸውን እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ የማዕከሉን በይፋ መከፈትና ሥራ መጀመር ባበሰሩበት ወቅት እንደተናገሩት የማዕከሉ መከፈት ለሠራተኞቹ ምርታማነትና ለህፃናቱ ደህንነት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ድርጅቱ ባለው አቅም በቀጣይ በማዕከሉ የተጓደሉ ነገሮች እየታዩ እንደሚስተካከሉ ገልፀዋል፡፡