ስልጠናው በዋናነት መከላከል ላይ ያተኮረና የድርጅቱን የሥራ ባህሪ ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም በከተማችን አዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች “የእሳት አደጋ ተከስቶ የማይተካው የሰው ህይወትና ንብረት አወደመ” የሚል ዜና በተደጋጋሚ እየሰማን እንገኛለን፡፡ ለአደጋው መንስኤ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች ቢጠቀሱም ከግንዛቤ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚኖረው የቅድመ መከላከል ተግባር አለመኖር ብሎም አደጋው ሲከሰት ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ተገቢ አለመሆን በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለህትመት ሥራው የሚጠቀምባቸው እንደ ወረቀትና ኬሚካል ያሉ ግብዓቶች በቀላሉ ተቀጣጣይና የእሳት አደጋን ሊያባብሱ የሚችሉ እንደመሆናቸው መጠን የድርጅቱ ሰራተኞች በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ራሳቸውንም ሆነ ድርጅታቸውን ከእሳት አደጋ ሊጠብቁ ይገባል በሚል በየዓመቱ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡
የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ስልጠናው ከየካቲት 04-08/2016 ዓ.ም ለተከታታይ አምስት ቀናት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት በመጡ አሰልጣኞች ተሰጥቷል፡፡
በሥልጠናው ከየሥራ ክፍሉ የተውጣጡ ሃያ ስምንት ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የእሳት አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ብሎም በጅምር ያለ እሳትን ለማጥፋት የሚያስችሉ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ልምምድን የተካተተበት እንደነበር የድርጅቱ የሰው ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ታመነ ዘውዱ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ታመነ ገለፃ በስልጠናው ሰልጣኞች በድርጅቱ እሳትን ለመፍጠር ምቹ የሆኑ ተቀጣጣይ ነገሮች በብዛት ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ሰራተኞችን በጅምር ያለ እሳትን ለማጥፋት የሚያስችል ስልጠናን በማሰጠት የቅድመ ጥንቃቄው ሥራ መሰራቱ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነና ሥልጠናውን የተካፈሉ የድርጅቱ ሰራተኞች በንድፈ ሀሳብና በተግባር ያገኙትን ሥልጠና ለራሳቸውም በመጠቀም ለሌሎች ሰራተኞች ግንዛቤ በመፍጠር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ያነጋገርናቸው የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከድርጅቱ የሥራ ባህሪ አንፃር እንዲህ አይነት ስልጠናዎች መሰጠታቸው ግንዛቤን ከማሳደግ አንፃርና አደጋ እንዳይከሰት ከመከላከል፣ ከተከሰተም ትክክለኛውን እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ተገኝተው ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት የሰጡት የድርጅቱ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ (ሀብት አመራር ዘርፍ) አቶ መለሰ ስሜነህ እንደገለፁት ድርጅቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራና ይህም ስልጠና የዚህ ማሳያ መሆኑን ገልፀው ሰልጠኛች በንድፍና በተግባር የሰለጠኑትን በድርጅቱ እሳት አደጋ እንዳይከሰት በሚያስችል በቅድመ መከላከል ላይ በማተኮር ተግባር ላይ እንዲያውሉት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አክለውም በስልጠናው ወቅት ሰልጣኞች ያስተዋሏቸው በድርጅቱ የእሳት አደጋ ስጋት የሆኑ አካባቢዎች ላይ አፋጣኝ የማስተካከል ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡