ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ለአካባቢ ፅዳት አገልግሎት የሚውሉ ስድስት ጋሪዎችን ጥር 16/2011ዓ.ም በተካሄደ መርሃ-ግብር በስጦታ አበርክቷል፡፡
ለፅ
ዳት ሥራ አገልግሎት የሚውሉ ጋሪዎችን ያስረከቡት የድርጅቱ ድጋፍ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በላይ ኪዳኑ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ይህንን ሥራ እንዲያከናውን ባቋቋመው የሥራ ክፍል አማካኝነት በዕቅድ በማካተት ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን የመደጋፍ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ደጋፊ የሌላቸውን ህፃናትን የመደገፍ፣በጫማ ማስዋብ ሥራ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ወጣቶችን የመደገፍ ሥራ እንዲሁም ለአካባቢው ወጣቶችን ድርጅቱ ባቋቋመው የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የነፃ ትምህርት ዕድል በመስጠት ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በድርጅቱ ተቀጥረው እንዲሰሩ የማመቻቸትና ሌሎች ተጓዳኝ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነ ጠቁዋል፡፡
አቶ በላይ አያይዘውም ለአራዳ ፍፍለ ከተማ ለወረዳው የተበረከቱት ለፅዳት ሥራ የሚውሉ ጋሪዎች በአካባቢ ፅዳትና ውበት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ማህበራት ትልቅ ድጋፍ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ ከድርጅቱ በስጦታ የተበረከቱ ጋሪዎች ለታለመላቸው ዓላማ ውለው ውጤቱን ማየት እንደሚያስፈልግና ወደፊትም ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶች እስቀረቡ ድረስ በተመሳሳይ የድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሺሻይ ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው መንግስት የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማከናወን በጀት መድቦ እንደሚሰራ ገልፀው ነገር ግን በመንግስት በጀት የማይሸፈኑ ሥራዎችን በአካባቢው ከሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር እንደሚያከናውን ገልፀው በወረዳው አካባቢ የሚያፀዱ ማህበራት ለፅዳት አገልግሎት ሥራ የሚውል የጋሪ ችግር ስለገጠማቸው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትን ትብብር መጠየቃቸውንና ስድስት ትላልቅ ጋሪዎች አሰርቶ በመስጠቱ አመስግነው በቀጣይም ለሚኖሩ የልማት ሥራዎችን ከድርጅቱ ጋር በጋራ የመስራት ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል ፡፡