የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2013 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2014 እቅድ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ነሐሴ 04 ቀን 2013 ዓ.ም በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገመገመ፡፡ በግምገማው የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሃብታሙ ኃይለሚካኤል፣ የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል እና የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንዲሁም የሚመለከታቸው የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡
የድርጅቱ የኦፕሬሽን፣ የለውጥ ስራዎች፣ የፋይናንስ፣ የፕሮጀክት፣ የኮቪድ 19 አፈፃፀም፣ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት እንዲሁም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች በድርጅቱ የዕቅድ ዝግጅት ፕሮጀክት ጥናትና ክትትል አገልግሎት ኃላፊ በሆኑት አቶ መኮንን አበራ በኩል ቀርበዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ውስጥ 239,295,680 ብር የሚያወጣ ምርት ለማምረት ታቅዶ 290,388,288 ብር የሚያወጣ ምርት ለማምረት ተችሏል፡፡ የተጣራ ሽያጭ 460,184,000 ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 554,175,727 ብር ለማግኘት የተቻለ ሲሆን ከታክስ በፊት 161,163,320 ብር ለማግኘት ታቅዶ 177,441,817ብር ለማግኘት መቻሉ በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በኤጀንሲው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገረመው ቀኖ በበኩላቸው በድርጅቱ በበጀት ዓመቱ እቅድ አፈፃፀም ሂደት የታዩትን ጠንካራ ጎኖች፣ በአፈፃፀም የታዩትን ክፍተቶች እና በቀጣይ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በግምገማው የማምረት ዓቅም አጠቃቀም፣ የምርት፣ የሽያጭና የትርፍ አፈፃፀም ከእቅድ በላይ መፈፀም፣ የድርጅቱን ፋይናንስ ጤናማ መሆንና የድርጅቱን ሀብት በአግባቡ ስራ ላይ እየዋለ መሆኑን በእቅድ አፈፃፀም ግብረ መልስ ላይ ተመላክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ድርጅቱን መደገፍ፣ በአራት ዋና ዋና የሪፎርም አጀንዳዎች (የአመራር አቅም ግንባታ እና ተኪ አመራር መፍጠርን፣ የአሠራር ሥርዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሻሻል፣የገበያ ተወዳዳሪነት እና የሀብት ተመላሽ እና ኢንቨስትመንት) አቅዶ በመስራት አፈፃፀሙ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የ2012 በጀት ዓመት ሂሳብ በIFRS መሠረት ተመርምሮ የውጭ ኦዲት ሪፖርት መቅረቡ እና ሪፖርቱም ከስህተት የፀዳ (Clean) መሆኑ፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በእቅድ መሰረት መፈፀሙ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር፣ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት እና የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በጠንካራ ጎን የተገለፀ ሲሆን የፕሮጀክቶች እና ካፒታል በጀት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም አስተዳደራዊ ወጪ ከፍ ያለ መሆን በአፈፃፀም የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን አቶ ገረመው ገልፀዋል፡፡
የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እና የመለዋወጫ ችግሩን ለመፍታት ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር በመወያየት እና ምርታማነትና የምርት ሽያጭ ገቢን ማሻሻል፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የድርጅቱን የማምረት አቅም ማጎልበት እና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የተጠናከረ ክትትል ማድረግ፣ የውጪ ምንዛሪ ክትትል በማድረግ የካፒታል ግዢዎችን በዕቅዱ መሠረት እንዲከናወኑ ጥረት ማድረግ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቅድመ መከላከል ሥራዎች በመስራት እና የጥገናን አቅምን በማጠናከር የመሳሪያ ብልሸት ድግግሞሽን መቀነስ፣ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት አሰራሮች ማዘመን ላይ ትኩረት መስጠት፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በዕድሜ በመለየት መሰብሰብ ላይ የተጠናከረ ርብርብ ማድረግ እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል በቀጣይ በድርጅቱ በኩል ትኩረት ተሰጥቶባቸው መከናወን እንዳለባቸው በውይይት መድረኩ ተገልጿል፡፡
በቀረበው የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አስተያየትና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል እና የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሃብታሙ ኃይለሚካኤል እንደተናገሩት ድርጅቱ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ የበጀት ዓመቱን እቅድ በማሳካት ትርፋማ መሆኑ ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ እንደሆነ ገልፀው ለአፈፃፀሙ ውጤታማነት የቦርዱ፣ የማኔጅመንቱና የሰራተኞች የተቀናጀ ስራ የጎላ ሚና እንደነበረው ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የኦፕሬሽን ስራዎች ውጤታማነት፣ ወጪ መቀነስ ፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በእቅድ መሰረት መፈጸም፣የቦርድ አመራሮችና አባላት ድርጅቱን ለመደገፍ እያደረጉት ያለውን ጥረት፣ ሂሳብን ወቅታዊ ማድረግ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ውጤት መቀየር እና ድርጅቱ ትርፋማ ሆኖ መቀጠሉ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ድርጅቱ ከፍተኛ ውድድር ያለበት ዘርፍ ውስጥ ሆኖ በ2013 በጀት ዓመት ያስመዘገበው ውጤት በጣም ጥሩ በሚባል የአፈፃፀም ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ክቡር አቶ ሃብታሙ ገልፀው ድርጅቱ በቀጣይ በጀት ዓመት ከዚህ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በሚያደርገው ጥረት በኤጀንሲው በኩል ያልተቆጠበ ድጋፍ ለማድረግ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡