ድርጅቱ ውስጥ ያለው መናበብና ሰላም የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ስኬት ምክንያት በመሆኑ ይህንኑ በማስቀጠልና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመከተል ስኬቱን ሊያስቀጥል አንደሚገባ ተገለፀ

የድርጅቱ የ2013 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ዙርያ የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ማኔጅመንት፣ ቡድን መሪዎችና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች በተገኙበት ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ውይይት ተካሄዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የኦፕሬሽን፣ የለውጥ ስራዎች፣ የፋይናንስ፣ የፕሮጀክት፣ የኮቪድ 19 አፈፃፀም፣ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት እንዲሁም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች እና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ዋና ዋና ተግባራት በድርጅቱ የዕቅድ ዝግጅት ፕሮጀክት ጥናትና ክትትል አገልግሎት ኃላፊ በአቶ መኮንን አበራ በኩል ቀርበዋል፡፡

በመድረኩ የድርጅቱ 100ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ በዓል አከባበር የተዘጋጀው ዕቅድ የቀረበ ሲሆን የበዓል አከባበሩ ድርጅቱ ያለፈባቸውን የጉዞ ሂደት ከመዘከር ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነነትን መወጣትን ታሳቢ ባደረገ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

በእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና በቀጣይ በጀት ዓመት እቅድ ዙርያ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተነሱ ጉዳዮች ዙርያ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የድርጅታችን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንደተናገሩት በ2013 በጀት ዓመት ለዕቅዱ መሳካት የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በጋራ ተናቦና ተረባርቦ በመሥራት የተገኘ መሆኑን፤ ዕቅዱ መሳካት ያጋጠሙን የውስጥ እና የውጭ ችግሮች በቀጣይ በጀት ዓመት እንዳይደገም መርሃ-ግብር በማዘጋጀት መስራት፤ግብዓትና መለዋወጫዎችን ለማሟላት በትኩረት መስራት፤በየስራ ክፍሉ የተከለሱትን ስታንዳርዶች እስከ ታች ድረስ በማውረግ ተግባራዊ እንዲሆን ክትትል ማድረግ፣ወጪ ቆጣቢ የሆነ አሰራር መከተል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈፃሚው አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት አዳዲስ ማተሚያ ድርጅቶች ወደ ኢንዳስትሪው እየገቡ በመሆኑ ውድድሩ ጠንካራ ስለሆነ ከዚህ በፊት የነበረውን የተለመደ አሰራር ተከትለን መሄድ ከውድድር ውጭ ስለሚያደርገን የተሻለ የአሰራር ስርዓትና ቴክኖሎጂ በመጠቀም በውድደሩ አሸናፊ ሆኖ መውጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦች ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ የገለፁት አቶ ሽታሁን ከፊት ለፊታችን የተደቀኑ ችግሮች በጋራ ሆነን በመስራት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የድርጅታችን የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል እንደተናገሩት ድርጅቱ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ የበጀት ዓመቱን እቅድ በማሳካት ትርፋማ መሆኑ ሊመሰገን እንደሚገባ ገልፀው ለአፈፃፀመሙ ውጤታማነት የቦርዱ ፣ የማኔጅመንቱና የሰራተኞች የተቀናጀ ስራ ውጤት መሆኑንና ድርጅቱ ውስጥ ያለው መናበብና ሰላም የበጀት ዓመቱን ዕቅድ አፈፃፀም እንዲሳካ ምክንያት በመሆኑ ይህንኑ በማስቀጠልና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመከተል ስኬቱን ሊያስቀጥል አንደሚገባ  ገልፀዋል፡፡ አቶ ወርቁ አያይዘውም በ2013 በጀት ዓመት የነበሩንን ክፍተቶች ዙርያ የጋራ መግበባት ላይ የተደረሰ መሆኑን ገልፀው  በቀጣይ እንዳይደገሙ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ድርጅቱ ከፍተኛ ውድድር ያለበት ዘርፍ ውስጥ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት ክቡር አቶ ወርቁ ድርጅቱ በቀጣይ በጀት ዓመት ከዚህ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በሚያደርገው ጥረት  በቦርዱ በኩል ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡