በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የዓለም የፀረ ሙስና ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

 በዓለም 18 ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ 17 ጊዜ በተከበረው በዓል ላይ የድርጅቱ ሰራተኞች መልካም ስነምግባር ተላብሰው ሙስናን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ከአመራሩ ጐን መሰለፍ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ፡፡

በሥነ ምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያበሚል መሪ ቃል ህዳር 29 ቀን 2014 . በተከበረው የዓለም የፀረ ሙስና ቀን ክብረ በዓል ላይ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት፤ ቡድን መሪዎች አስተባባሪዎችና ከየስራ ክፍሉ የተውጣጡ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

በዕለቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትና በዓሉን አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ሥራ እፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለበሥነ ምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያየሚለውን የበዓሉን መሪ ቃል አስታውሰው ስነምግባርና መልካም አስተዳደር ማስፈን እንዲሁም ብልሹ አሰራርን ማስወገድ በሀገር ብሎም በድርጅት ደረጃ የሚኖረውን አዎንታዊ ሚና ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም እንደዚህ ያሉ በዓላትን ሲከበሩ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በማጤን ለመፍታት በማቀድና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተሰሩ ሥራዎችን በመገምገም ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የአመራሩ ሚና እና ቁርጠኝነት ሙስናን ለመከላከል ግንባር ቀደሙን ሚና የሚጫወት መሆኑን ከግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባ በበዓሉ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ስነምግባር ዳይሬክተር አቶ መለሰ በቀለ ገልፀው ያለሰራተኛው ተሳትፎ የአመራሩ ሥነ ምግባር መጠበቅ ብቻ ውጤት ያመጣል ተብሎ እንደማይታሰብና ሠራተኛው መልካም ስነምግባር ተላብሶ ሙስናን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ከአመራሩ ጐን መሰለፍ እንደሚጠበቅበት በመክፈቻ ንግግራቸው አስገንዝበዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም መንግስት በአሁኑ ጊዜ በሥነምግባር ግንባታ ላይና በሙስና መከላከል ላይ በማተኮር በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ እና በድርጅቱ የሚከናወኑ ሥራዎች በሙሉ የመልካም ስነምግባር እና የሙስና መከላከል ውጤቶች በመሆናቸው በድርጅታችን ያለው መልካም ውጤት ሁሉ የአመራሩና የሰራተኛው ርብርብ የታከለበት ስለሆነ መልካም ስነምግባር እና ሙስና መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከተሰራ ውጤቱ ያማረና ከፍተኛ በመሆኑ በቅንጅት የሙስና መከላከል እና የሥነምግባር ግንባታ ሥራ ላይ እናተኩር የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በበዓል አከባበሩ ላይየስነምግባርና የሞራል እሴትን በመገንባት እና ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል የኢትዮጵያ አፈፃፀም ከፀረ ሙስና ኮንቬንሽን አኳያ፣እናየስነምግባርና የሞራል እሴት ግንባታ ሙስናን ለመከላከልየሚል ርዕስ ያላቸው ሰነዶች በዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን በእለቱ በተካሄደው የጥያቄና መልስ ውድድር አሸናፊዎችን ሽልማት እና ከየስራ ክፍሉ በስነምግባር ለተመረጡ ሰራተኞች የእውቅና ደብዳቤ ተበርክቷል፡፡