በጦርነቱ ለተፈናቀሉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች የተበረከቱ የድጋፍ ቁሳቁሶችን በስፍራው በመገኘት ለማስረከብ የተቋቋመው ግብረሃይል በደማቅ አሸኛኘት ወደ ስፍራው አቀና፡፡
ሀገራችን የገጠማትን ጦርነት በድል እስክታጠናቅቅ በግንባር በመዝመት እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አመራርና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊታችንና ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ደጀንና አለኝታነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ ከማኔጅመንት አባላት እና ከመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች የተውጣጣ ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመደገፍ ወደ ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ እና አፋር ታህሳስ 16 ቀን /2014 ዓ.ም ጉዞ ጀምሯል፡፡
በሽኝት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሸታሁን ዋለ እንደተናገሩት 100ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ ያለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራር በመፍጠር ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች የሚውል በጀት በዕቅድ በመያዝ ዜጎችን የመደገፍ ስራውን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እየፈፀመ እንደሚገኝ አስታውሰው ሀገር በእንዲህ ያለ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ስትገኝ አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ድጋፉ ከሠራተኛውና ከማኔጅመንቱ የአንድ ወር የደመወዝ መዋጮ ብር 8,980,000 /ስምንት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሺ ብር/ ፤ለ100ኛ ዓመት የድርጅቱ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ለድግስ ዝግጅትና ለሌሎች ኘሮግራሞች ሊውል የነበረውን ብር 1,000,000 /አንድ ሚሊዮን ብር/፤ የመሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር ብር 200,000 /ሁለት መቶ ሺህ ብር/፤ከሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ብር 50,000 /ሀምሳ ሺ ብር/ እና ከሠራተኞች ክበብ አገልግሎት ኮንትራክተር /ብር 10,000 /አሥር ሺ ብር/ በድምሩ ብር 10,240,000 /አሥር ሚሊየን ሁለት መቶ አርባ ሺ ብር/ መሰብሰብ እንደተቻለ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል ለመከላከያ ሠራዊታችን በሁለት ዙር ብር 5,500,000 /አምስት ሚሊየን አምስት መቶ ሺ ብር/ ድጋፍ የተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽታሁን አሁን ላይ በተጨማሪ ለ3ኛ ጊዜ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ብር 4,500,000 /አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር/ ድጋፍ በቀጣይ በመከላከያ ኘሮግራም ተይዞ ተፈፃሚ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው በድምሩ ብር 10,000,000 /አሥር ሚሊዮን ብር/ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከተሰበሰበው ገንዘብ ቀሪው ብር 5,740,000 /አምስት ሚሊዮን ሰባት መቶ አርባ ሺ ብር/ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ድጋፉ በዓይነት የሚሰጥ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሽታሁን ምን ዓይነት አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ከብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን መረጃ በመውሰድ እንዲለይ ተደርጐ ድጋፉም በሶስት አካባቢዎች ማለትም ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ እና አፋር እንዲደረግ ተወስኗል ብለዋል፡፡ የድጋፉም ዓይነት ዱቄት፣ ዘይት፣ አልሚ ምግብ እና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ አገልግሎት ፓድ በመግዛት በዓይነት ድጋፉ የሚሰጥ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ሰራተኞች ከገንዘብ መዋጮ በተጨማሪ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን የተለያዩ አልባሳት በማምጣት እንዲሰበሰቡ የተደረገ ሲሆን የተሰበሰበው ልብስ የወንድ፣የሴትና የልጆች በሚል ተለይቶ በሶስት ቦታ ተካፍሎ የሚሰጥ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በግንባር በመዝመት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል 23 ሰራተኞች ተመዝግበው እየተጠባበቁ መሆናቸውን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው የድርጅቱ ማኔጅመንት እነዚህ ሰራተኞች ላሳዩት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ታላቅ አክብሮትና ምስጋና እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የድርጅቱ የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋአለም ኃይሉ በበኩላቸው እንደተናገሩት በአገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን ለመደገፍ ሰራተኞች ላሳዩት በጎ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊታችን ደም ለመለገስ ፍቃደኛ መሆናቸውን በመድረኩ ላይ የተገለፀ ሲሆን የደም ልገሳ መርሃ-ግብሩ ብሔራዊ የደም ባንክ በሚያወጣው ፕሮግራም መሰረት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡