የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትና የድርጅቱን አሁናዊ ገጽታ ባስቃኘ መልኩ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ድርጅቱ 100 ዓመታትን የተሻገረ የካበተ ልምድና ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ ጠንካራ የሥራ ባህል ቢኖረውም በህትመት ዘርፍ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ የህትመት መሳሪያዎችን ባለቤት አለመሆኑ ራዕይውን እውን ለማድረግ ተግዳሮት እንደሆነበት ተገልጿል፡፡

በሀገራችን አንጋፋውና የህትመት ብርሃን ፈንጣቂው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከመስከረም 14 እስከ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል፡፡

የአከባበር እቅድ በማዘጋጀት፤በማኔጅመንት እና በሥራ አመራር ቦርድ በማስገምገም ወደ ትግበራው የገባው ድርጅቱ በእቅድ የያዛቸውን ኩነቶች በተሳካ ሁኔታ በማሰናዳት ደማቅና ተደራሽ በዓልን አሳልፏል፡፡

በበዓል አከባበር እቅድና ትግበራ ላይ ከሥራ አመራር ቦርድ በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገና ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ትኩረቱ ያደረገ ብሎም የድርጅቱ የሀገር ባለውለታነት ባሳየ መልኩ መከበሩን ማሳየት ተችሏል፡፡

መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም በደማቅ የመክፈቻ መርሃ ግብር የተጀመረው በዓል አከባበር በሃገራችን በተከሰተው ጦርነት የተፈናቀሉና የተጎዱ ወገኖችን መደገፍ አንዱ ተግባሩ ነበር፡፡ ለበዓል ድግስ ይውል የነበረን በጀት በመቀነስ፤ከሰራተኛውና ማኔጅመንቱ የአንድ ወር ደሞዝ ፤ከመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ፤ ከሰራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር እንዲሁም ከሰራተኞች ክበብ ኮንትራክተር የተለገሰን ገንዘብ ላይ ተቀናሽ በማድረግ በሃገሪቱ ሶስት አካባቢዎች በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል፡፡

በደቡብ ጎንደር፤ ደቡብ ወሎ በአፋር ክልል ለሚገኙ ወገኖች ስፍራዉ ድረስ በመሄድ ድጋፍ መደረጉ ቀደም ሲል የተጀመረው የድርጅቱ የሀገር ባለውለታነት ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳይ በጎ ተግባር ነው ተብሏል፡፡

ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖች አለኝታነቱን በተግባር ያሳየው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጀት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሌላኛው የድጋፍ ትኩረቱ ነበር፡፡

የሀገራችንን ህዝብ በመተሳሰብ የመኖር ዘመናትን የተሻገረ ባህልን በመናድ ሃገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞችን በመመከት የሀገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ህይወቱን እየገበረ ለሚገኝው የሃገር መከላከያ ሰራዊታችንን ደጀንነቱን በተግባር ለመግለጽ በሶስት ዙሮች ያደረገው የ10ሚሊዮን ብር ድጋፍ አንዱ ማሳያ ነበር፡፡

ታህሳስ 28 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደው እና በርካታ የድርጅቱ ሰራተኞች የተሳተፉበት ለሀገር መከላከያ እና ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተደረገ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ወቅታዊ ቅኝቱን የጠበቀ የበዓል አከባበሩ ድምቀት ነበር፡፡

በደም ልገሳ መርሀ ግብሩ የተሳተፉ ሰራተኞች በእንዲህ ባለው ሰብአዊ ተግባር ላይ በመሳተፍ የድርጅቱ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማክበራቸው የተለየ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልፀው ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ ሲያከናውን የኖረውን የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባር ሳያቋርጥ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚያደርገው ጥረት ላይ በንቃት ለመሳተፍ ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን እምብዛም በትምህርትና ስልጠና ያልተደገፈ እንዲሁም የጥናቶች መዳረሻ ያልሆነው የህትመት ዘርፍ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ይገለጻል፡፡

ከድርጅቱ አንጋፋነት አንጻር በዘመናት ውጣ ውረዶች እንዲሁም አሁን ያለበትን ደረጃ በተጨባጭ በሚያሳይ መልኩ ያስጠናው ጥናታዊ ጹሁፍ ከድርጅቱ ባሻገር የሃገሪቱን የህትመት ዘርፍ ተግዳሮቶች ያሳየ ነበር ተብሏል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፉ ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር እና የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና አባላት፤የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚና የማኔጅመንት አባላት፤ ባለድርሻ አካላት ፤ደንበኞች ፤የህትመት ግብዓት አቅራቢዎች እና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች በተገኙበት ቀርቧል፡፡

በእለቱ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሃብታሙ ኃይለሚካኤል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ብራና ፍቀው ቀለም ቀምመው፣በእጅ ጽፈው ያቆዩዋቸውን መንፈሳዊና ታሪካዊ ሰነዶች ወደ ህትመት በማስገባት ዘመናዊ የህትመት ሥራ ፈር ቀዳጅና የሀገር ባለውለታ ተቋም መሆኑን አስታውሰው 100ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ቢሆንም፣ የዕድሜውን ያህል ወቅቱን እየተከተለ እራሱን በቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሠራር አብቅቷል ብሎ መናገር እንደማይቻልና ትርፋማ ሆኖ የዘለቀው አመራሮቹና ሠራተኞቹ ኋላ ቀር ማሽኖቹን በውስጥ አቅም በመጠገንና ፈጠራን በማከል ያላሰለሰ ጥረት በማድረጋቸው ነው ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ሃብታሙ ድርጅቱ አቅሙን በሰለጠነ የሰው ኃይል፣በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሠራር በማጠናከር በገበያው ውስጥ ተመራጭ ሆኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ አክለውም በእለቱ የሚካሄደው የፓናል ውይይት በዚህ ረገድ ሠፊ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበት ለቀጣይ ዕቅዱ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ጠቃሚ ነጥቦችን ያስገኛል የሚል እምነት እንዳለቸውና በውይይት የሚገኙትን ግብዓቶች በመጠቀም፣ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደር እና የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓትን አጠናክሮ በመቀጠል ምርታማነትና ትርፋማነትን የበለጠ እንዲያሳድግ አሳስበው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደርም ተገቢውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ከድርጅቱ ጎን እንደማይለይ ገልፀዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው ድርጅቱ በሀገራችን የህትመት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ከ100 ዓመት በፊት የጀመረውን የህትመት ሥራ በየጊዜው ወቅቱ የፈቀደውን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና አቅሙን በማሳደግ በመደበኛና በሚስጢራዊ ህትመት ለደንበኞቻችን የህትመት አገልግሎት በመሰጠትና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ካስቆጠረው ዕድሜ አንፃር በቴክኖሎጂ አጠቃቅም፣ በአደረጃጀትና በአሠራር በሚጠበቀው ደረጃ አቅሙን ባለማሳደጉ የደንበኞችን ፍላጎት በተሟላ ሁኔታ ከማርካት አኳያ ውስንነቶች የሚታዩ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሀገር ውስጥና በድርጅታችን ሊታተሙ የሚገባቸው በርካታ ህትመቶች በውጭ ሀገር የሚታተሙ በመሆናቸው ሀገራችን ካላት ውስን የውጭ ምንዛሪ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በውጭ ሀገር ታትሞ ለሚገባ ህትመት ወጪ የሚደረግበት ሁኔታ ይታያል ብለዋል፡፡

አክለውም የድርጅቱን ውስንነቶች በመቅረፍ ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻልና ደንበኞችን በማርካት ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ካስቆጠረው እድሜ አኳያ የሚመጥን ለማድረግ በውይይቱ የተገኙ የመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉና በውይይቱ ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ታሪክ ዳሰሳ፣ ተስፋና ተግዳሮት፤ በተሰኘው ጥናታዊ ፅሁፍ የሀገራችን ህትመት ተግዳሮቶች እና በህትመት ዘርፍ ያሉ የሰለጠነው ዓለም የደረሰባቸው ዘመናዊ የህትመት ማሽነሪዎች ከድርጅቱ አሁናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሁኔታ ጋር በንጽጽር ቀርበዋል፡፡

በጥናቱም የዓለም የህትመት ዘርፍ እያንቀሳቀሰ ያለው ግዙፍ ካፒታል፤በሃገራችን የህትመት ቴክኖሎጂውንና የሰለጠነ የሰው ኃይል ባለመሟላቱ ወደ ውጪሀገር በመላክ የሚታተመውን የህትመት ውጤቶች በሃገር ውስጥ በማሳተም የሚወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማስቀረት እንደሚቻል የተጠቆመ ሲሆን የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትን የዘመናዊ ህትመት ማሽነሪዎችና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃብት ማሟላት የሃገራችንን ህትመት ኢንዱስትሪ ማዘመን እንደሆነ ተገልጻል፡፡

ከጥናቱ በኋላ በነበረው የፓናል ውይይት ጥናቱንና አጠቃላይ ድርጅቱን የተመለከቱ ጥያቄና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ውይይቱን የመሩት ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ፤አቶ ሽታሁን ዋለ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና አቶ ይታገሱ ጌትነት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል በጥናታዊ ፅሁፉ የተካተቱና በውይይቱ የዳበሩ የድርጅቱ ችግሮችን የጋራ በማድረግ ለመፍትሄዎቹ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጠባብ መድረክ በመገናኘት መወያየቱ ለመፍትሄው እንደሚያግዝ ስለታመነበት በቀጣይ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ከፓናል ውይይቱ በመለስ ከጥር 19-21/2014 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት የተካሄደው የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በርካታ ጎብኝዎችን አስተናግዷል፡፡

ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀውን የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በጋራ የከፈቱት ሲሆን የድርጅቱን ታሪካዊ ዳራ የህትመት ቴክኖሎጂ እድገት ደረጃና የማህበራዊ ሃላፊነት ተሳትፎ የታዩበት ነበር፡፡

ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም የድርጅቱ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መዝጊያ መርሃ-ግብርና እና የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ተማሪዎች የምረቃ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡

በበዓል አከባበር ማጠቃለያው ላይ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት፣ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር አመራሮች፣ የድርጅታችን ሠራተኞች፣ ተመራቂዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ካሳ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በሀገሪቱ በህትመት ዘርፍ ሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግርን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ባካበተው የረዥም ጊዜ የህትመት ሥራ ልምድ እና ባለው አደረጃጀት ላይ በመመስረት፣ በ2007 ዓ.ም የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መክፈቱን አስታውሰው የድርጅቱን ምርታማነትና ትርፋማነት ለማረጋገጥ እንዲቻልም በህትመት ዘርፍ ከሚታየው ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብሮ የሚሄድና ቴክኖሎጂውን ሊያንቀሳቅስ የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ እንደሆን ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ በመደበኛነት ከሚያሰለጥናቸው ተማሪዎች በተጨማሪ ከ1 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ሰልጣኞች አጫጭር ኮርሶች መስጠቱን የተናገሩት የኮሌጁ ዳይሬክተር በቀጣይ ኮሌጁ በህትመት ዘርፍ በዲግሪ መርሃ-ግብር የማሰልጠን ዕቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ድርጅቱ 100ኛ ዓመት የምሰረታ በዓሉን ሲያከብር በከፈተው ኮሌጅ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን በደረጃ ሶስት 31 ሰልጣኝ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ከፍተኛ ደስታ ይሰማዋል ያሉ ሲሆን ተመራቂዎችና ቤተሰቦች የድካማችሁን ውጤት የምታዩበት የምረቃ ጊዜ ላይ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የበዓል አከባበርና የተማሪዎች ምረቃ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ለ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው ለዕለቱ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያለችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ድርጅቱ ህልውናውን በማስቀጠል ለዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው በየጊዜው ያጋጠሙትን ችግሮች መፍትሔ በመስጠት በድርጅቱ ያገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ ሠራተኞች፣ ድርጅቱን የመሩ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ባደረጉት አስተዋጽኦና ጥረት መሆኑን ገልፀው ከማሽን ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮች በዘላቂነት መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ ሠራተኛው ያለውን ልምዱንና ዕውቀቱን በመጠቀም በተለመደው ታታሪነትና ትጋት ማምረቻ መሣሪያዎችን በጥንቃቄ በመጠቀምና በመጠገን የበጀት ዓመቱ ዕቅድ እንዲሳካ ተገቢውን ርብርብና ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሀገራችን የህትመት ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ለመሆኑ እንደማሳያ ከሚገለፁ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው በሀገራችን በርካታ የመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲዎች የተከፈቱ ቢሆንም በአንዳቸውም ተቋም የህትመት ቴክኖሎጂ ትምህርት አንደማይሰጥና ድርጅታችን ይህንን ክፍተት በመረዳት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በመክፈት የሠራተኞችን ብቃት የማሳደግና ፍላጎቱ ላላቸው ዜጎችም ሙያውን እንዲማሩ ኮሌጁ ትምህርትና ስልጠና መስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ 100ኛ ዓመቱን ሲያከብር በሥራ ላይ ያለን ሠራተኞችና አመራሮች ድርጅቱ አሁን ያሉበት ችግሮች ተቀርፈውና ድርጅቱ በተሻለ ቴክኖሎጂና አሠራር እንዲደራጅ በማድረግ፣ አቅሙን በማሳደግ፤ የኢንዲስትሪ ሰላሙን በመጠበቅ፤ ምቹና ተመራጭ የሥራ ቦታ እንዲሆንና በደንበኞች ተመራጭ የህትመት ተቋም በማድረግ፤ የድርጅቱ አቅምና ገቢ አድጎ ሠራተኛው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ድርጅቱ ለሀገርና ለማህበረሰቡ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማሳደግ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ አድርገን እናስተላልፍ በሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተያያዘም የድርጅታችን የ100ኛ ዓመት በዓል አከባበር በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ጥረትና ርብርብ ላደረጉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ስፖንሰር ላደረጉ ድርጅቶችና ሌሎች በተለያየ መልኩ ተሳትፎና ድጋፍ ለነበራችሁ አካላት ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡