የሠራተኞች ዓመታዊ በዓል ሲከበር የድርጅቱ ውጤታማነት ላይ የላቀ አፈፃፀም ለነበራቸው የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚና ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች የዕውቅና ሽልማት ከሠራተኛው ተበርክቶላቸዋል፡፡
ህዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በተከበረው ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉልን ጨምሮ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፤ የማኔጅመንት አባላትና አጠቃላይ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በበዓል አከባበሩ የድርጅቱ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም፤የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም በድርጅቱ ስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ቀርቧል፡፡ አቶ መኮንን አበራ ባቀረቡት ዝርዝር አፈፃፀምና ዕቅድ ሪፖርት በ2015 በጀት ዓመት ድርጅቱ በምርት፣ በሽያጭና በትርፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንና በተመሳሳይም በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በምርት፣ በሽያጭና በትርፍ አበረታች ውጤት መመዝገቡን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የቀረበውን ሪፖርት እንዲሁም በድርጅቱ የተካሄደውን የመዋቅር ጥናትና የደመወዝ ማሻሻያ አተገባበር በተመለከተ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች በድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የመዋቅር ትግበራው ድርጅቱ የተሻለ ሥራ ሰርቶ አትራፊ ሆኖ እንዲዘልቅ በማሰብ የሥራ አመራር ቦርዱ መዋቅሩን በመገምገም ተግባራዊ እንዲሆን በመፍቀዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የማኔጅመንት አባላትና አጠቃላይ ሰራተኛው ምስጋናን አቅርበዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ቀደም ሲል በነበረው የአሰራር ሥርዓት ድርጅቱ የሚኖረውን የወጪ ጫና ተቋቁሞ በመዝለቅ ያቀደውን ዕቅድ ማሳካት ስለማይቻል ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የበዓል አከባበሩ ተሳታፊዎች በከፊል
ዋና ሥራ አስፈፃሚው በ2015 በጀት ዓመት በምርት፣ በሽያጭና በትርፍ ከነበረው ዕቅድ አንፃር የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ከፍ ያለ መሆኑንና ይህም በየደረጃው ባሉ የሥራ ኃላፊዎችና አጠቃላይ ሰራተኞች ውይይት ተደርጎበት የፀደቀ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አያይዘው ይህንን ከፍ ያለ ዕቅድ ለመፈፀም በድርጅቱ በኩል ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያ ግዢ ለመፈፀም አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው አሁን ላይ ባሉ ማምረቻ መሳሪያዎች ዕቅዱን ለመፈፀም እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊከናወኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች ያቀረቡ ሲሆን የሥራ ሰዓት አጠቃቀም፣ የሥራዎች ክትትልና ቁጥጥር፤ የሥራዎች ጥራትና የማስረከቢያ ጊዜ መጠበቅ፤ በሥራ ክፍሎችና በሰራተኞች መካከል ያለውን የሥራ ቅንጅት/ግንኙነት፣ለስራዎች አፈፃፀም የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት በዕለቱ ከተነሱት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ነበሩ፡፡
በበዓል አከባበሩ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ላይ የሠራተኛ ተወካይ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሁለት የቦርድ አባላት የሥራ ጊዜያቸው በመጠናቀቁ እና በአዲሱ መመሪያ መሰረት አንድ የሰራተኛ ተወካይ በማስፈለጉ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በዚህም መሰረት በሰራተኛ ከተጠቆሙት ሶስት እጩዎች መካከል አቶ ኩምሳ ከሮርሳ አብላጫ የድጋፍ ድምፅ በማግኘት በሥራ አመራር ቦርድ የሰራተኛ ተወካይ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በተያያዘም በድርጅቱ ሲያገለግሉ ቆይተው በ2016 በጀት ዓመት በጡረታ ለተገለሉና ለሚገለሉ አመራርና ሠራተኞች የምስጋና መርሃ ግብር ተከናውኖ በክብር ተሸኝተዋል፡፡

በሌላ በኩል በሰራተኞች ተነሳሽነት የድርጅቱ ውጤታማነት ላይ የላቀ አፈፃፀም ለነበራቸው የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እና ም/ል ዋና ሥራ አፈፃሚዎች አቶ ጌታሁን ነጋሽ እና አቶ በላይ ኪዳኑ በሠራተኞች የዕውቅና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን እውቅና የተሰጣቸው አመራሮች ድርጅቱ እያስመዘገበ ላለው የላቀ ውጤት መሰረት የሆነ በሳል አመራርና የድርጅቱን ህልውና ለማስቀጠል በየዘርፉ ላከናወኑት የላቀ አፈፃፀም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተያያዘም የአመራሮችን አቅጣጫ በመከተል የኢንዱስትሪ ሰላሙን በማስጠበቅ የድርጅቱ ውጤታማነት ላይ በትጋት እየሰራ ያለው አጠቃላይ የድርጅቱ ሰራተኛ በተወከሉ ሰራተኞች አማካኝነት የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የድርጅቱ ሠራተኞች ሽልማቱን ባስተባበሩት ኮሚቴዎች አማካኝነት ድርጅቱ አስጠንቶ ተግባራዊ ካደረገው የመዋቅር ጥናት በመነሳሳት የድርጅቱን ራዕይና ግብ ለማሳየት፣የተጣለባቸውን አደራ እንዲሁም ድርጅቱ የተቀበላቸውን ሥራዎች በስታንዳርድ መሰረት በመስራት በወቅቱ ለደንበኛ ለማስረከብ፣የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት በማክበርና በሥራ ቦታ ላይ ቀድሞ ለመገኘት፣ የትርፍ ሠዓት ሥራን ለማስቀረትና ለመቀነስ፣፤ የማምረቻ ግብዓቶችን በቁጠባ ለመጠቀም እንዲሁም በድርጅቱ ተደራራቢ ሥራዎች በሚኖሩበት ጊዜ በዘመቻ ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡
በበዓሉ ማጠናቀቂያ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል በ2015 በጀት ዓመት ድርጅቱ በምርት፣ በሽያጭና በትርፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንና በተመሳሳይም በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በምርት፣ በሽያጭና በትርፍ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀው ለዚህም የተሻለ አፈፃፀም የድርጅቱ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ጥረትና የሥራ ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑን በመግለፅ ድርጅቱን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ለድርጅቱ ውጤታማነት የሥራ አመራር ቦርዱ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡