የኢትዮጵያን የፓስፖርት አሠራር በማዘመን፤ በማንነት፣ በሰላማዊ ጉዞ እና በደህንነት ዙሪያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል የተባለ ስምምነት በተለያዩ ተቋማት መካከል ተፈርሟል፡፡
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት እና ቶፓን ግራቪቲ ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር፣ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እና የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻ እና ማከፋፈያ ድርጅት በጋራ የተቋቋሙት የአቅርቦትና አገልግሎት ሥራ እንዲጀምር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን የፓስፖርት አሰራር በማዘመን፣ አዲስ ለተነደፈው የኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርት የተሻሻሉ የደህንነት ባህሪያትን እና የተሻሻለ ቅልጥፍናን በማምጣት ረገድ ትልቅ እመርታ ይኖረዋል ተብሏል።
ለኢትዮጵያ የፓስፖርት ቴክኖሎጂ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን የሚያመለክት መሆኑም ተጠቁሟል።
በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ወደ ተሻለ የፓስፖርት አሰጣጥ ሂደት እንከን የለሽ ሽግግር ለማድረግ ቃል መገባቱም ተገልጿል። የማተሚያ ፋብሪካው በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚሆን ሲሆን ይህ ፈር ቀዳጅ ስምምነት በማንነት፣ በሰላማዊ ጉዞ እና በደህንነት ዙሪያ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መረጃ አመላክቷል።