ውይይቱ በመንግሥት የስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የኢኮኖሚ፣ የመሰረተ ልማት፣ የማኅበራዊ ልማት እና የአስተዳደር ዘርፎች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ ም/ዋና ሥራ አስፃፈፃዎች የማኔጅመንት አባላትና አጠቃላይ ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ሰነድ በድርጅቱ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ (ኦፕሬሽን ዘርፍ) አቶ ጌታሁን ነጋሽ ቀርቧል፡፡
የድርጅቱ ሰራተኞች እንደዜጋ በመንግስት በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ዙሪያ ተመሳሳይ ግንዛቤ ኖሯቸው ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ባለመው ውይይት የማክሮ ኢኮኖሚ፤ የኢኮኖሚ ዘርፎች፤ የመሰረተ ልማት ዘርፎች፤ የማህበራዊ ልማት ዘርፎች እና የአስተዳደር ዘርፎች አፈጻጸም ከዓለም አቀፍ እና ከአህጉራዊ ሁኔታዎች አንፃር በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል የድርጅቱ የ2016 በጀት ዓመት በ8 ወራት ጊዜ ውስጥ ከዕቅድ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት የተካተተበት ሪፖርት በድርጅቱ ስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ቀርቧል፡፡ የበጀት ዓመቱ 8 ወራት አፈፃፀም የበጀት ዓመቱን እቅድ ለመፈፀም አቅም የሚሆንና አበረታች መሆኑን የተገለፀ ሲሆን ይህንን ውጤት በማስቀጠል የበጀት ዓመቱ ዕቅድ እንዲሳካ ሠራተኞች ለዕቅዱ ተፈጻሚነት በተመደቡበት ሙያና የስራ ክፍል በሙሉ አቅማቸው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በቀረበው መወያያ ሰነድ ላይና በድርጅቱ የ8 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ሀሳብና አስተያየት እንዲሰጡ ለተሳታፊዎች በተሰጠው እድል መሰረት ተሳታፊዎች ላነሷቸው ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደገለፁት ከተካሔደው ውይይት ሠራተኞች በሀገራዊ የስድስት ወራት አፈፃፀም ዙሪያ በቂ መረጃ እንዳገኙ እምነታቸውን ገልፀው ሰራተኞች በድርጅቱ የሚያከናውኑት ጥረት የተሞላበት ሥራ እንደ ሀገር ለሚታየው ውጤት ግብዓት እንደሆነ እንዲሁም የበጀት ዓመቱ ቀሪዎቹ አራት ወራት ለድርጅቱ ዓመታዊ ዕቅድ ስኬት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ለድርጅቱ እቅድ መሳካት በትኩረት፣ በመናበብና በርብርብ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡