የ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በወረዳው ለተለዩ 100 የአካባቢው ነዋሪዎች ለእያንዳንዳቸው የ2000 ብር ስጦታ አበርክቷል፡፡
ሚያዚያ 21 2016 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው የድጋፍ መርሃ-ግብር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፣በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አስተዳደር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል እሸቴ የድርጅቱና የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የድርጅቱ ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሐይማኖት ተገኝተዋል፡፡
የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባሩን አጠናክሮ የቀጠለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እንደ ቀድሞ ለፋሲካ በዓል በአካባቢው የሚገኙና በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑ አረጋውያን በዓሉን በጥሩ ሁኔታ ያሳልፉ ዘንድ ቀደም ሲል ሲደረግላቸው ከነበረ የምግብ ግብዓት የዓይነት ድጋፍ ለየት ባለ መልኩ የ2000 ብር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አስተዳደር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል እሸቴ ለአረጋውያኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በተለያዩ ሰው ተኮር ሥራዎች ከጎናቸው በመሆን የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ የሚገኘውን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትን አመስግነዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ድርጅቱ የመንግስትና የህዝብ እንደመሆኑ መጠን ለሀገር ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር አቅም በፈቀደ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን በዕቅድ በማካተትና በጀት በመመደብ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ አክለውም የተደረገው የበዓል መዋያ ድጋፍ ድርጅቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን አክብሮት እና የወገን አለኝታነት መግለጫ መንገድ መሆኑን ገልፀው የመልካም በዓል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘም በእለቱ በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ከተደረገው የድጋፍ መርሃ ግብር ባሻገር የተለያየ የጤና እክል ኖሮባቸው ከቤታቸው መውጣት ያልቻሉ አቅመ ደካማ አረጋውያንን ታሳቢ በማድረግ የድርጅቱ ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ አገልግሎት ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ተክለሐይማኖት ከወረዳው ባለሙያዎች ጋር በመሆን የበዓል መዋያ ድጋፉን ቤት ለቤት የማድረስና አረጋውያኑን የመጎብኘት ሥራ ተከናውኗል፡፡